Get Mystery Box with random crypto!

( ግብዣው ፤ ቅጽ 2) (በእውቀቱ ስዩም) ጓደኛየ ዘፈን መስራት ካቆመ አስር አመታት ያለፈው ድምጻ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

( ግብዣው ፤ ቅጽ 2)
(በእውቀቱ ስዩም)
ጓደኛየ ዘፈን መስራት ካቆመ አስር አመታት ያለፈው ድምጻዊ ነው:: ዋና ስሙ ፋኑኤል ሲሆን ለደህንነቱ ሲባል " ዘነመ" እያልሁ እጠራዋለሁ፤ ከቀናት ባንዱ ሰንበት “ወለላ “ ምግብ ቤት በረንዳ ተቀምጠን አስተናጋጅ እንጠብቃለን፤ አንዲት እንዲያው በደፈናው የአፈወርቅ ተክሌን ስእል የመሰለች ሴት ከፊታችን ብቅ አለች ::
“ አድናቂ ነኝ”
“ በጣም አመሰግናለሁ” አልኩ፤
“ ፈርምልኝ”
“ ምን ላይ ልፈርም?’
አንባቢያን ሆይ ! ባታምኑኝም ከመናዘዝ ወደ ሁዋላ አልልም፤ እየተሽኮረመመች “ ጡቴ ላይ “ አለችኝ :: እኔም ከኢትዮጵያ ባህል ጋር ላለመጋጨት፤ ከጡቷ ጋራ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ላለመቆራረጥ ፤ የጡት ማስያዣዋ ላይ ፈረምኩ::
“የት ነው እምትኖሪው?”
“ ሪችመንድ ነኝ! ከሁለት ሳምንት በሁዋላ አገር ቤት እሄዳለሁ”
“እቃ ይዘሽልኝ ትሄጃለሽ?”
‘ ኖ ፕሮብሌም! ይሄ ላንተ የማደረገው ትንሹ ነገር ነው “
“ለኔስ?” አለ ዘነመ፡:
‘ ቤቴ ራት እንድጋብዛችሁ ፍቀዱልኝ ! ቆንጆ ጭቅና ጥብስ መስራት እችላለሁ”
“ደስ ይለናል” አለ ጓደኛየ ተሽቀዳድሞ፤
ትንሽ ቆይቶ “ መጣሁ ! “ አለና ሹልክ ብሎ ወጣ፤
“አግብቷል ?” ስትል ጠየቀችኝ፤
“ አራት ጊዜ አግብቶ ፈቷል ”
“አንተም ፈት እንደሆንህ ሰምቻለሁ፤ ”
“ ልክ ነሽ! ስራ ፈት ነኝ”
“ ሸበላ ነገር ነው”
“ ጠባዩስ ብትይ ! ዘንዶ ያለምዳል”
ወደ ፊልም ቢቀየር ሁለት ሲዝን የሚወጣው ወሬ ስናወራ ከቆየን በሁዋላ ፤
“ እኔ እምልህ እስቲ ስለ እቃው ንገረኝ” አለችኝ::
“ ጎን ለጎን ሆነን ስንሸና እንዳየሁት ከሆነ አስተማማኝ እቃ ነው ያለው “ አልኳት::
“ እኔ እንኳ የጠየኩህ አገር ቤት ትወስጅልኛለሽ ስላልከኝ እቃ ነበር ! ብቻ መረጃ አይናቅም”
ከማፈሬ የተነሳ የምመልሰው ቸግሮኝ ሳልጎመጉም ጓደኛየ ሁለት ኪሎ ስጋ እና አንድ ወይን ፤ ይዞ ተመለሰ;
እሳት ጎርሳ ፤ ጭስ ተፍታ ወቀሰችው፤
“ አፒታይት እና ስጋ ከኛ ነው፤ ካንቺ ሙያ ብቻ ነው እሚጠበቅብሽ ” ብሎ አለዘባት ::
ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ወደ ቤትዋ መንዳት ጀምራለች፡: እኔና ዘነመ በርሱ መኪና ተከተልናት " ሸበላ " ነው ያለቺውን ስነግረው “ ባትለኝም፤ ልጂቱ እንደተዝለፈለፈችልኝ ገና ከመጀመርያም አውቄዋለሁ፤ ቤት ስንደርስ እንደፈረደብህ የሆነ ምክንያት ፈልገህ ዞር ትላላህ” አለኝ::
“ የት ነው ዞር የምለው ?” አልሁ ያለ የሌለ በሽቄ::
“ ወይ ሞቴል ትይዛለህ ! ካልሆነ የፈረንጅ ደጀሰላም ፈልገህ ትተኛለህ ”
ሁለት ሰአት ያክል ነድተናል:: የምትኖርበት ኮንደሚኒየም በር ላይ ስንደርስ መጥርያውን ተጫነቸው፤ በሩ ሲከፈት አንድ የጠወለገ ራስታ ሰውየ ከውስጥ ብቅ አለ:: ከወገቡ በላይ የተራቆተው ሰውነቱ በንቅሳት ተዥጎርጉሮ የጥምቀት ሽመል ይመስላል፤ ሰላምታ እንኳ ሳይመጸውተን ስጋውንና ወይኑን ተቀብሎን ወደ ውስጥ ገባ፤ ተከትለነው ስንዘልቅ የጫማ፤ የሀሺሽ እና የድህነት ጠረን ተቀበለን::
ሰጋውን ከምኔው ጠብሶ አደረሰው?! አበላሉን ስመለከት፤ ላለፉት ሶሰት ቀናት እህል እንዳልቀመሰ መገመት አላቃተኝም፤ እኛን እንደ እንግዳ ቀርቶ እንደ ፖስተኛ እንኳ አልቆጠረንም፤
ዘነመ ፤ጥግ ይዛ ወይናችንን እምትቀመቅመውን ጉደኛ እየተመለከተ “ ሸኚን” የሚል ምልክት አሳያት፤
ሶስታችን ድምጻችንን አጥፍተን አንድ አራት ደረጃ ወረድን፤
ከጠጉሬ እስከ ጥፍሬ የወጠረኝን ሳቄን ለመቆጣጠርና የወዳጄን ፊት ላለማየት መታገል ጀመርኩ፤
ብዙ አልራቅንም፤ ዘነመ ርምጃውን ገታ አድርጎ ፤ ለመላው የህንጻው ነዋሪ በሚሰማ ድምጽ
“ እናትሽ ትረዳና ባል እንዳለሽ ለምን አልነገርሽኝም?” ብሎ ጮኸባት!
ልጂቱ፤ዘና ፤ ረጋ ብላ የመለሰችውን ልጻፈውና ታሪክ ይፍረደው፤
“ አገሩ super busy ስለሚያደረግ ብዙ ነገር ትዘነጋለህ! ባል እንዳለኝ ራሱ ትዝ ያለኝ አሁን ነው”
"

ከወደዱት ለወዳጆ ያጋሩ
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19