Get Mystery Box with random crypto!

‹‹በቂ›› ስንት ነው? (How much is enough?) ጊዜ በቂ አይደለም፡፡ ሕይወት በቂ አይ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

‹‹በቂ›› ስንት ነው? (How much is enough?)

ጊዜ በቂ አይደለም፡፡ ሕይወት በቂ አይደለም፡፡ ዕውቀት በቂ አይደለም፡፡ ገንዘብ
በቂ አይደለም፡፡ ደስታችንም በቂ የሚባል ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ ሞልቶ እየፈሰሰ
ያለው መከራችን፣ ችግራችንና ሐዘናችን እንጂ ደስታችን ብቃት ላይ አልደረሰም፡፡
ወዳጅነትም ሆነ ዝምድና በቂ ነው አይባልም፡፡ የዚህ ዓለም ፍቅርም በቂ
አይደለም፡፡ አብዛኛው የዘንድሮ ወዳጅነትም ሆነ ዝምድና በወረት ያጠረ እንጂ
ዘላቂ አይደለም፡፡ ኑሮ በቂ አይደለም፡፡ ሞት በራሱ በቂ አይደለም፡፡ እንደሰው
የመኖር ፍላጎት ዕድሜ ከበቂ በታች ነው፡፡ ሰው ራሱ ሳይበቃ ነው የሚያልፈው፡፡
ገንዘብ በቃኝ ያለ የሰው ልጅ እስካሁን አላየንም፤ በታሪክም ዶሴ ተመዝግቦ
የተሰነደ የለም፡፡ በቂ የሚለው ቃል በራሱ በቂ አይመስለኝም፡፡ ቃላቱ ሁለት
ቢሆንም መለኪያውና መስፈሪያው የትየለሌ ነው፡፡ ‹‹በቂ›› የሚለውን ቃል
በሁለት ፊደል ብቻ መወከል ፍትሐዊ አይደለም፡፡ በቂ እንደየሰዉ መስፈሪያ ከፍም
ዝቅም ይላል እንጂ እቅጩን ሆኖ አያውቅም፡፡ የምንም ነገርን መስፈሪያ
በግምትና በስምምነት ወይም ከዚህ እስከዚህ የምንለው እንጂ በራሲ በቂ የሆነ
አይደለም፡፡ በቂ የመጠን ጉዳይ ነው፡፡ መጠንን መመጠን ደግሞ የመጣኙ ፋንታ
ነው፡፡ አንዱ ከመጠኑ አስበልጦ አሙልቶ ሲያፈሰው ሌላው ደግሞ ከመጠኑ
በታች አድርጎ ያጎድለዋል፡፡ ሰው ራሱ በቂ ሆኖ ተፈጥሯል ወይ ብለን ብንጠይቅ
እኔ ሰው በቂ ወይም ብቁ ሆኖ አልተፈጠረም ባይ ነኝ፡፡ ይልቁንስ ብቁ ይሆን ዘንድ
እንዲችል ልዩ የአዕምሮ በረከት ተበርክቶለታል፡፡ በቂን የሚያበቃው በአዕምሮ
የበቃው ብቻ ነው፡፡
ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ ሲናገር፡-
‹‹እግዚአብሔር ፍፁማን አድርጎ ሊፈጥረን ይቻለው ነበር፡፡ ሆኖም ግን እንደዚያ
ይፈጥረን ዘንድ አልወደደም፡፡ ይልቅስ ለፍፅምናችን የተዘጋጀን አድርጎ ፈጠረን
እንጂ፡፡›› ይላል፡፡
እውነት ነው! ሰው Ready-Made አይደለም፡፡ አካሉ ነው ተሰርቶ የተዘጋጀው፡፡
ብቃቱን፣ አስተሳሰቡን፣ አኗኗሩን፣ ዕውቀቱን፣ መክሊቱን፣ ወዘተ ተጨባጭና
ተጨባጭ ያልሆኑ እሴቶቹን የሚፈጥረው ራሱ ሰውየው ነው፡፡ ሰው አዕምሮ
ቢሰጠውም ሁሉ ነገር ተሰርቶለት ያለቀለት ፍጡር አይደለም፡፡ ራሱ በራሱ ላይ
ሊያሟላቸው የሚገቡት ሺ ጎዶሎ ነገሮች አሉበት፡፡ በአዕምሮው አስቦና
ተመራምሮ በእጆቹ ሊያከናውናቸው የሚገቡ እልፍ ተግባራት ይጠብቁታል፡፡
ኑሮ ያልበቃን፣ ገንዘብ ያልበቃን፣ ዕውቀት ያልበቃን፣ ደግነት ያልበቃን፣ ፍቅር
ያልበቃን የምንፈልገውን የእውነት ስለፈለግነው ሳይሆን ሌሎች ስለፈለጉት ብቻ
እኛም ሰለፈለግነው ነው፡፡ አዎ ብዙዎቻችን የምንፈልገውን የማናውቀው
ፍላጎታችን የተመሰረተው በሌሎች ፍላጎት ላይ በመሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ
መሠረታው የሰው ልጅ ፍላጎት ተመሳሳይ ቢሆንም አፈላለጋችንና ፈልገን
የምናመጣበት መንገድ የተለያየ ነው፡፡ የሆድ ጉዳያችን፣ ርሃባችን፣ ጥማችን
ስሜቱ የጋራ ቢሆንም መንፈሳዊ ረሃባችንና ጥማታችን፣ እንዲሁም
አስተሳሰባችንና ግባችን የተለያየ ነው፡፡ የብቃት መለኪያችንም የሚለየው ‹‹በቂ››
የሚለው መስፈሪያ እንደየአስተሳሰባችን አንድ ወጥ ባለመሆኑ ነው፡፡
ሮበርት ስኪደልስኪ የተባለ ፀሐፊ እንዲህ ይላል፡-
‹‹የምንፈልገው ከመጠን በላይ ስለሆነ አይደለም፡፡ ነገር ግን እኛ የምንፈልገው
ሌሎች ከሚፈልጉት የበለጠ እንዲሆን ስለምንሻ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ
ሌሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ የሚፈልጉት እኛ ከምንፈልገው በላይ እንዲሆን ነው፡፡
ይሄም መጨረሻ ወደሌለውና አሸናፊው ወደማይለየው ፉክክር ውስጥ
ከትቶናል፡፡(“It is not just we want more but that we want more
than others, who at the same time want more than us; this
fuels an endless race”)›› ይለናል፡፡
አዎ! ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹በመጠን ኑሩ!!›› የሚለው ወዶ አይደለም፡፡ ከዕውቀት
ሁሉ መጠንን ማወቅና ‹‹በቂ››ን መገንዘብ ዋነኛ የህይወት ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡
ከመጠን ያነሰም ሆነ የበዛ ጣጣ አለው፡፡ ከበቂ በላይም ሆነ ከበቂ በታች
ሁሉቱም አይጠቅሙም፡፡ በቂ መካከለኛው ነጥብ ነው፡፡ በቂ መጠን ነው፤ መጠን
ደግሞ ማስተዋል ነው፡፡
ሰሞኑን “Philosophy’s Big Questions” በሚል ርዕስ ለሕትመት የበቃ አንድ
መፅሐፍ አለ፡፡ ፀሐፊው በዚሁ መፅሐፍ የፍልስፍና ከባባድ ወይም ቁልፍ
ጥያቄዎች ናቸው ብሎ ከዘረዘራቸው ስምንት ጥያቄዎች ውስጥ አንደኛው ‹‹በቂ
ስንት ነው?›› የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ‹‹በቂ›› የሚለው ቃል አንድምታው በወጉ
የተተነተነ አይደለም፡፡ ለማንኛውም ለጥያቄዎቹ መልስ ካላችሁ ወይም ደግም
ጥያቄዎቹን ማሰላሰል ከፈለጋችሁ ፀሐፊው በዚሁ መፅሐፍ ‹‹ከባባድ የፍልስፍና
ጥያቄዎች›› ብሎ በስምንት ምዕራፍ ከፍሎ የተነተናቸው ጥያቄዎች
እንደሚከተሉት ናቸው፡-
1) እንዴት ነው መኖር ያለብን? (How should we live?)
2) ዕውቀት ምንድነው? (What is knowledge?)
3) እውነታ መነሻ አለው ወይ? (Does reality have a ground?)
4) ንቃተ ሕሊና ሊገለፅ ይችላል? (Can consciousness be explained?)
5) የምናከናውናቸው ነገሮች ሁሉ የእኛ ጉዳይ ብቻ ናቸው? (Is anything we
do really up to us?)
6) ለምንድነው መጥፎ ነገሮች ጥሩ ሰዎች ላይ የሚደርሱት? (Why do bad
things happen to Good people?)
7) በቂ ስንት ነው? (How much is enough?)
ለወደፊቱ ትውልድ የምናወርሰው ዕዳ ምንድነው? (What do we owe
future Generations?)
ወዳጄ ሆይ.... ‹‹የብልፅግና ዋነኛ ግብ መሆን ያለበት እንደገብጋቦች ማከማቸት
ሳይሆን ሕይወትን በምድር ላይ በደስታ ማኖር ነው›› እንዲል ፈላስፋው
ወልደሕይወት መጠንህን እወቅና ብቃትህን ተጎናፀፍ፡፡ የምትፈልገውን ሁሉ
ለማሟላት ስትል ዕድሜህን አትጨርስ፡፡ ከምትፈልገው ይልቅ የሚያስፈልግህን
ምረጥ፡፡ ማግበስበስን ሳይሆን መመጠንን ልመድ፡፡ የ‹‹በቂ›› መስፈሪያህን
በቅተህ አግኘው፡፡
በቂ ደስታ! በቂ ሕይወት! በቂ ዕውቀት! በቂ ሃሳብ! በቂ ፍቅር! በቂ ተስፋ! በቂ
ፍላጎት! በቂ ግብ!
ቸር ጊዜ!
____________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)

ዕለተ እሁድ መስከረም ፱ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም.

ከወደዱት ለወዳጆ ያጋሩ
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19