Get Mystery Box with random crypto!

(ሚካኤል ኤርሚያስ) እንዴት ባዳ ሆንን....? እንዴትስ አልገባን የሚበልጥብንን እንዴትስ አላየን | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

(ሚካኤል ኤርሚያስ)

እንዴት ባዳ ሆንን....?
እንዴትስ አልገባን የሚበልጥብንን
እንዴትስ አላየን የሚያሻግረንን

ከህይወታችን መፀሀፍ ላይ
ከተገነጠለች አንዲት ነጠላ ገፅ
ብላፍ ብዳክር
ብወጣና ብወረድ ላወጣበት ህፀፅ

አንዳች አላገኘው ጎሪጥ ሚያተያየን
ኸረግ አልገባኝም ምንድነው የለየን

እፎይ ማ'ያ ጎጆ ብንናፍቅ
ከእ'ኛ ወዲያ ላንል ፈቀቅ

ምን ባትጨክኝ ባትሸሺ ሕም ባልርቅሽ
እኔም አንቺም ባዳ ለፍቅሬ ለፍቅርሽ

እንዴት ሆነ ይሄ......?

ትዝ ይልሽ እንደሆን ...
ንጋት ...
ከወፎች ጋር ተሻምተን
ጠይም ጠሀይ ስትወጣ
በለሆሳስ እንዳላቀነቀንን
ምሽት ...
ባለጅራታሙን የሰሜንኮከብ ተመልክተን
አፍችንን በእጃችን ገርበብ አድርገን
አጃኢብ ብለን ተፈጥሮን እንዳላደነቅን

ትዝ ይልሽ እንደሆን ......

እወድሻለሁኝ ስል
ያልነበረችገደል ማሚቱ ለእኔ ስትል መጥታ ድምፀቴን እንዳላስተጋባች
ምነው ዛሬ ስንበክን እንዴት አሁን ስንመክን ልትሸመግለን አልመጣች

ታ.ዘ.ብ.ኳ.ት

ያኔ ...
ናፍቆተ እንባን ስናነባ
ፍቅር በእሳት ልምጭ ሲገረፈን
ስለመውደድ ደረታችንን እየደቃን
ሀዘን ሳይሰብረን ተፍነክንከን
መከፍት ላይ እንዳልሳቅን
ስንቱን እንዳልተሻገርን

የመነጠልን ቅዝምዝም ዱላ
በትእግስት እንዳልመከትነው
አሁን ...ፅኑ ፍቅራችንን
ምንድን አቅሙን ነፈገው ....?

መልስ አለሽ ?
እኔ የ.ለ.ኝ.ም
ኸረግ አ ል ገ ባ ኝ ም ....

ቀድሞ..
የነፍስ ሀቅሽ ከነፍስ ሀቄ ተዋዶ
አንቺነትሽ ከእኔነቴ ተጋምዶ
መጠላለፍችን ላይጥለን
ሀረግ ይመስል እንዳላጎለበተን
አሁን...
ለነጠላ መጋፈጡን
ለየቅል ኩታ ብርድና ውርጩን ማሳለፉን
እንዴት ቻልን.......?

ለፍቅርሽ ለፍቅሬ እንዴት ባዳ ሆንን....
መልስ አለሽ ...
እኔ የለኝም
ኽረ እነደውም ...አልገባኝም ...
መልስ አለሽ ...

#ሚካኤል ኤርሚያስ