Get Mystery Box with random crypto!

#########ትንታ########### ደም እያባበለ ጣር ከሚያሽሞነሙን የዘመን ቁስል ላይ ስንት | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

#########ትንታ###########

ደም እያባበለ ጣር ከሚያሽሞነሙን የዘመን ቁስል ላይ
ስንት እንባ ዘነበ ሳግ ከሚደውረው የልባችን ሰማይ??
በረከሱ ነፍሶች ጎባጣ ወገብ ላይ ድንጋይ ተቀርቅቦ
መዳህ ሳይጀመር መንከባለል ሆነ ሸክም ሸክምን ስቦ።
መከረኛ ዛሬ ለቅጽበት ሽራፊ እንቅልፍ ቢዞረው
ሰመመኑ ባሰ ከህልም ተኳርፎ ቅዠት ተዋረሰው።
በጽልመት ብርሀን በሰካራም ስሌት በዛር በቅሎ ሽምጥ
በነፍሰጡር ቅስቻ በውቃቢ ጥሪ በእልፍ መሀን ምጥ
ነፍስሽ ስታቃስት ማርያም ማርያም ይላል እድምተኛሽ ከቦ
ከእግሮችሽ ሰፈረን ዳናሽ በዳናችን በሲቃ ተከትቦ።
መሻር ያላደለው እዥ የተዋደደው መግል ያዘለ ቁስል
ምርኩዝ ያልሽው እንጨት ህማም ተጠፍሮ አንቺን ነው እሚያማስል።
ከትብታብ ጎዳና ከአስማተኞች መንደር ጻድቅ ቢገኝልሽ
መተት ለመደ አሉ ከደጁ ፈውሶ ከእልፍኙ ሊገድልሽ።

እህህ እህህ እንደው እህህ ነው።

እህህ ልበለው ቃል ቅኔ የለውም ግራ ነው ነገሩ
የአድባሬን እሮሮ የጦቢያዬን ስቃይ ለአዝማሪው ንገሩ
ይዘምር ይዝፈነው የመገፋት ልኳን በቅኝት ይዘርዝር
ልብ እየተደቃ ሙሾ ይውረድላት ባለ ቀን ይጨፍር።

ወትሮም

ከኔ ቢጤ ደጃፍ ከአዳፋ መቀነት ከለማኝ ቤት ጓዳ
የቁንጣን ጭቅቅት የግፈኛ ሳቅ ነው በገፍ የሚቀዳ።
ሁሉን አሜን ብላ ለተጎናበሰች ብሶተኛ ሀገር
ስብራቷ ሊድን ተራው ሲደርሳት ነው ወጌሻው እሚሰበር።
መባው ሳይጓደል አዝመራው ሳይነጥፍ መሸመን ቧገታ
ጥምሽን ላይሽረው የሰጡሽ ጭላጭ ነው ያስያዘሽ ትንታ!!
መርምሪው አለሜ በጭላጭ ከመሞት ጥም ገደላት ያምራል
ሸምጋይ ከተገኘ ቀን ከቀን ሲታረቅ ድርቅ ያረሰርሳል።
በዘመን ፍርርም በቃል ኪዳን ስሌት ነፍስ ተረክዞ
የኢትዮጵያን ምድር መቼ ነው የሚረግጠው ሙሴችን ተጉዞ??

ርግጥ ነው አልክድም፦

የሙሴ ባለችው ታምረኛ በትር በቀጣት ነው ልምዷ
የአካሏን ህቅታ በተስፋ ማሰር ነው የዚች ሀገር ገዷ።
ከሳብዕ የራቀ ማሳረጊያ ያጣ የፈተና ግዕዝ
ምስካይ ነበርሽ ያኔ የፊትሽ ላይ ቆዳ ማዳትን ሳይበርዝ።
አለም ነበርሽ ያኔ የአዲስ ኪዳን እልፍኝ የአብርሃም ጓዳ
እኔ ላውዛሽ ያለ ከለጋስ ልቦናሽ ወዝሽን ሳይቀዳ።
ፊደል ነበርሽ ያኔ የሰማዩ ጥዑም ልሳን ባለ ቆብ የኔታ
A ና B ሳይጻፍ ሀሁለሉ ወርዶ ከፊደል ገበታ!!

ዛሬስ?????????

ዛሬስ እንደምን ሆንሽ ያንን መንሰራፋት ምን ገመድ አሰረ?
ምንኛ ቢሰብኩሽ ያሰረውን ኪዳን ልብሽ ወረወረ
በማን ልክ ተሰፍሮ ከደርባባ ቀሚስ እርቃን ተመረጠ?
በስንኩል ገበያ አሞሌና ጠጠር ግብር ተላወጠ!!

ዛሬማ፦

የወረት የወረት የክንንብ ሆኗል ዱአና ፀሎቱ
ለበረከት ሳይሆን ሆድ ለመሙላት ሆነ እሚበላ መክለፍቱ።

ዛሬማ፦

ጥቁር ሆኖብሻል የፀዳል ቀሚሱ የመሞሸሪያሽ ጨርቅ
ከምዕራቡ አለም እንዳሻው እሚደወር እንዳሻው እሚለቀቅ።

ዛሬማ፦

ልክሽ እንዲህ ለካ የቀን ወለፈንዲ የአልማዝ ገለባ
ጨቅላሽን አውርደሽ ሞች አዝለሽበታል በነተበ አንቀልባ።
አሸወይናን ቀዳ የሽማግሌ አዘን የህጻናት ለቅሶ
ከእልፋ አንበሳ መሀል ተኩላ ከበረ የበግ ለምድ ለብሶ።

ዛሬማ፦

ትላንትና ነገ በዛሬ ሰንሰለት እየተጠፈ
ትዉልድ የሚያብላላው የመከራ በቀት ቅኔ እየዘረፈ
አለን እስከዛሬ ነፍስያችን ናውዛ በባሩዱ ሽታ
በዛለ ጉሮሮ አካል እየሳለ በዘመን ትንታ!!!!!


29/02/2014
ሳሮናዊት እንድሪስ

ከወደዱት ለወዳጆ ያጋሩ
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19