Get Mystery Box with random crypto!

ክፍል ፬ ለ2 ቀን ይቆያል ተብሎ የተከፈተው የሥዕል አውደርእይ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል። አንድ ቦታ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ክፍል ፬

ለ2 ቀን ይቆያል ተብሎ የተከፈተው የሥዕል አውደርእይ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል። አንድ ቦታ ላይ ቆሜ በተርታ የተደረደሩ ሥዕሎችን የሚያዩትን ጥቂት ሰዎች እታዘባለሁ። ይሄኔ ነበር ከኋላየ...
"የኔን ምስል ብፈልገው አጣሁት ምነው ለአውደርእይነት አልመጥንም?" የሚል ድምፅ የሰማሁት

ልቤ ምቷ ሲጨምር ታወቀኝ ፈጣሪየ ሆይ!እሱ ራሱ ነው? ቀስ ብየ ዞርኩኝ የማይታመን! ራሱ ነው! ራሱ! አሮን ራሱ አሮን እጅጉ!
እጁን ለሰላምታ ዘረጋልኝ ሰላም ተባባልን።
አንዳንድ ነገሮችን እያወራን ቆየን ንግግሮቼ ሁሉ የተጠኑ እየመሰሉብኝ ተጨነቅኩ።

"ትንሽ ለማየት ሞክሬ ነበር አሁን ደግሞ ባንቺ መሪነት ባያቸው ደስ ይለኛል" አለኝ
አብረን ማየት ጀመርን ጥቂቶቹን እንዳየን ጓደኛየ ወደእኔ ስትቀርብ አየኋት

"ተዋወቂው እሱኮ ነው"

"እሱ?" አለችኝ በአይኗ ጭምር እየጠየቀች

"አወ አሮን ይባላል"

"ኦኬ ሰላም አሮን መአዛ እባላለሁ ስለተዋወቅን ደስ ብሎኛል" ጣልቃ ገባሁና

"አሮን ብቻ አደለም አሮን እጅጉ ነው"
"ኦ.....በእውነት ስላገኘሁህ በጣም ደስ ብሎኛል" ብላ የመደነቅ እና ለእኔም የማድነቅ ፊት አሳይታን "መልካም ጊዜ" ብላን አለፈች።

ሥዕሎችን እየተዘዋወርን በምናይበት ሰአት በድንገት አንዱ ሥዕል ላይ አፍጥጦ ቀረ ካጠገቡ ቆምኩ

"ዋ.....ው በጣም ነው የወደድኩት"

"በእውነት?"

"የእውነት አንደዚ አይነት ቀልቤን የገዛ ስራ አይቼ አላውቅም እባክሽ ልግዛው?"

"እንዴ ይሄን ያህል? ምኑ ነው የሳበህ? ጎልቶ የሚታይ ነገር የለውምኮ"(ሀሳቡን ለመስማት እንጂ ስራውን ማጣጣሌ አልነበረም)

"ትቀልጃለሽ ልበል? እኔስ እሱን አይደል እንዴ የወደድኩት እርጋታውን ረ...ጋ ያለ ነው ከጫፍ እስከጫፍ ፤ እኩል ነው ጩኸቱም ዝምታውም ፤ እኩል ነው የደመቀውም የፈዘዘውም ፤ የትኛውም ቦታ ላይ ተለይቶ ልታይ ልታይ የሚል ፉክክር ውስጥ አልገባም ስታይው እረፍት እና የልብ ሰላም ይሰጥሻል" ብሎ ትንሽ ፀጥ ካለ በኋላ

"የምር እገዛዋለሁ" አለ ለራሱ በሚመስል አነጋገር በዚህ ጊዜ ሌላዋ ጓደኛየ ሜሪ መጣችና ከእሷ ጋርም አስተዋወቅኩት ቀጥየም በዚህኛው አውደርእይ የማስጎብኘት እንጂ የመሸጥ ፍላጎት እንደሌለን ተመልካቾች ከወደዱት ግን ስቱዲዮ እየመጡ እንዲገዙ እንደምናደርግ ነገርኩትደ እሱም በቀልድ መልኩ

"ካላችሁ እሺ እስከዛም ሥዕሉን የማስቀምጥበትን ግድግዳ እየጠረግኩ እቆያለሁ" አለኝ

አንድ ጥግ ላይ ቆመን ስናወራ ከመጣ ጀምሮ ሲከነክነኝ የነበረውን ጥያቄ አነሳሁለት
"እኔ የምልህ እንዴት ግን እዚህ እንደሆንኩ አውቀህ መጣህ?"

"ምነው መምጣት አልነበረብኝም"

"አይ እንደዛ ለማለት ሳይሆን..." እንደማፈር አረገኝ ባልጠየኩት ኖሮ!
አልፎ አልፎ ብቻ ብልጭ የሚያረጋትን ፈገግታውን አሳየኝና

"የዛን ቀን ስልክ እንኳን ሳንለዋወጥ ስለቀረን ዳግመኛ አላገኛት ይሆን? እያልኩ ሳስብ ነበር ግን እንዳነበው የሰጠሽኝ መፅሀፍ ውስጥ(ፈገግ እያለ) ሁለት የመግቢያ ካርዶችን አገኘሁ ከዛም ስለአንድ አውደርእይ እንዳነሳሽልኝ ትዝ አለኝ ስለዚህ የት እንደሆንሽ አወቅኩ ማለት ነው"

"በነገራችን ላይ የዛን እለት እንደተመለስኩ ነበር ከጓደኛየ ተቀብየ መፅሀፍህን የጨረስኩት በአጨራረሱ ስላላሳፈርከኝ አመሠግናለሁ" አልኩት ፈገግ ብሎ ምስጋናየን ተቀበለ ሲስቅ ፂም አልባ ፊቱ ላይ የምትወጣው ዲምፕል ታምራለች
ቁመቱ ረጅምም አጭርም የሚባል አይነት አይደለም ከእኔ በጥቂቱ ረዘም ይላል። ውፍረቱ ከቁመቱጋ በተመጣጠነ በሚመስል መልኩ ነው ያለው። ፊቱ ላይ እንደው ለምልክት ያህል እንጂ ይሄ ነው የሚባል ፂም የለውም። ለመልኩም ሊነገርለት የሚችለው ሲስቅ የምትወጣው ዲምፕል እና በስርአት የተቀነደበ የሚመስለው ቅንድቡ ነው። አረንጓዴ የሚመስል ሹራብ እና ጅንስ ሱሪ አድርጓል። በእጁም ቀለል ያለች ማስታወሻ ደብተር ይዟል ቅዳሜ ቅዳሜ ከ6-8 ሰአት የሚተላለፍ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ እንደሆነም ነግሮኛል።

መገናኘታችን ቀጠለ መቀጣጠር፣ መገናኘት፣ስለተለያዩ ርዕሶች ማውራት፣ መከራከር፣መሳቅ፣መተከዝ የጋራ ግብራችን ሆነ። በቃ ጓደኛሞች ሆንን አንድ ቀን አንድ መናፈሻ መሳይ ቦታ ውስጥ ቁጭ ብለን ስናወራ

"እስኪ ዛሬ ስለፍቅር አውራኝ" አልኩት

"ስለ ፍቅር ምን?"

"የፈለከውን ለምሳሌ ላንተ እንዴት ይገለፃል? ግን በመጀመሪያ እንድትመልስልኝ የምፈልገው ለመሆኑ የምር አለ እሱ ነገር?"

"በፈጣሪ መኖር ታምኛለሽ አይደል? እሱ በፈጠራቸው ድንቅ ነገሮች ሁሉ ታምኛለሽም ታደንቂአለሽም አይደል? ሲመስለኝ ፈጣሪ ራሱ ከሰጠን ነገሮች በጣም የሚወደው ፍቅር የሚባለውን ነገር ይመስለኛል ለምን? ካልሽኝ በጣም ንጹሕ ስለሆነ ለኔ እስካሁን ፍቅር የለም ለማለት የሚያስደፍር አጋጣሚ አላጋጠመኝም ለነገሩ አለ ለማለትም በቂ አደለሁም ግን እግዚአብሔር እስካለ ድረስ ፍቅር የማይኖርበት ምክንያት አይታየኝም
እንዴት ትገልፀዋለህ ላልሽው
ፍቅር የሆነ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። የማይገባ ግን ደሞ ደስ የሚል፤ እያሳመመሽም የሚያስቅሽ፤ እያዳከመሽም የሚያበረታሽ ነገር ባጭሩ አንድን ከራስሽ ውጭ የሆነን አካል የሆነ ዋጋ መስጠት ነው ብየ አስባለሁ ቤተሰብሽን፣ሀገርሽን፣ጓደኞችሽን..."

"አይ እንደሱማ ካረግነው ይሰፋብናል እስኪ ስለአፍቃሪና ተፈቃሪ አውራኝ ግን ቆይ እስኪ ላንተ ከመውደድ እና ከመወደድ ከማፍቀርና ከመፈቀር የቱ ይበልጥብሀል?..."

"እ... ማንም ሰው ይወዳል ግድ ነው መውደድ ደስ ይላል ስትወጂ ከነፍስሽ ይሆንና መኖር ትጀምሪያለሽ ፤ ለሌላ ማሰብን ትጀምሪያለሽ ፤ መጨነቅ ታበዣለሽ።እንደኔ እንደኔ መውደድ ስትጀምሪ ነው ነፍስሽን የምታገኛት መጀመሪያ ያወቅሻቸውን እናትና አባትሽን ትወጃለሽ ከዛ ፈጣሪሽን ከዛ ጓደኞችሽን ስራሽን...
ስትወደጂ ደግሞ ሌላ ነገር ነው አንቺ ብቻ ለሰው ልሙት አትይም ላንችም ልሙት የሚል አለሽ ፤ አንቺ ብቻ ሳትሆኝ ባንቺ ምክንያት ነፍሱ የምትረካ ሰው አለሽ ፤ አንቺን ማሰብ መናፈቅ እንቅልፉን የሚያሳጣው ምግብ የማያስበላው ሰው አለሽ ፤ ከሌላው ሁሉ መርጦ አንቺን አንቺን የሚለው ስሜት ጭረሽበታል። ከዚ በላይ መታደል ያለ አይመስለኝም አንዳንዴ። መፈቀር ሁሉም ሊያገኘው የማይችል ፀጋ ነው

"ደስ ይላል የምር በእናትህ ቀጥል..."


...ይቀጥላል...

በአቤኒ የተጻፈ


ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19