🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

ማዳበርያ ( በእውቀቱ ስዩም) እንደ ድሮው ብዙ የሰውነት እንቅስቃሴ አላደርግም፤ ሲነሽጠኝ፥ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ማዳበርያ
( በእውቀቱ ስዩም)

እንደ ድሮው ብዙ የሰውነት እንቅስቃሴ አላደርግም፤ ሲነሽጠኝ፥ በሁለት ሳምንት አንድ ቀን ዢም ( gym) እሄዳለሁ፤ ወደ አዳራሹ እንደገባሁ አሰልጣኙ ሳያየኝ ፥ ኮቴየን “ ሳይለንሰር “ ላይ አድርጌ፥ ወደ ጥግ ሄድኩና የመጨረሻውን ሚጢጢ ዳምቤል አነሳሁ፤ ዳምቤሉ ከማነሱ የተነሳ ሁለት ራስ ያለው ትልቅ ቢስማር ነው እሚመስለው! ብዙም አልቆየም፤ የሆነ ድርብ ጭቆና የሚያህል መዳፍ ትከሻየ ላይ ወደቀ፤ ዞር ስል አሰልጣኙ ነው፤ እኔን ለማሰልጠን ሳይሆን ለማሰቃየት የተመደበ ነው እሚመስለኝ::

“ብረት ከማንሳትህ በፊት ማሟቂያ ስራ” ሲል አዘዘኝ::

“ ምን ልስራ?”

ትንሽ ሲያስብ ከቆየ በሁዋላ እንዲህ አለ፥
“ግራ እግርህን አንስተህ ፥ በማጅራትህ በኩል አሳልፈህ ተረከዝህን ሳም! “

እንደጀመርሁ አካባቢ ከጂሙ ሁለት ጊዜ በዊልቼር እየተገፋሁ ወጥቻለሁ::

ሰባት ፑሽአፕ ሰራሁና ሰባት ደቂቃ ከመስታወቱ ፊትለፊት ቆምኩ፤ እዚህ ጂም መምጣት ከጀመርሁ ወዲህ ለውጥ አለ፤ አንገቴ ዙርያ ሲክስ ፓክ አውጥቻለሁ፤ ጥቂት ቆይቶ፥ አሰልጣኙ “ ስኳት” አሰራኝ! ጂም ሄደህ ለማታውቅ አንባቢየ “ ስኳት” ማለት ሽንት ቤት ልትቀመጥ ፈልገህ ቁጢጥ ማለት ከጀመርህ, በሁዋላ ሽንት ቤቱ መበላሸቱን አይተህ ሀሳብህን ፥ቀይረህ ከመንገድ ስትመለስ ማለት ነው::

“ ስኳት ቢቀረብኝስ “ አልሁት የተንሸራተተ ዲስኬን ወደ ቦታው እየመለስኩ::

“ የግድ አስፈላጊ ነው” አለኝ አሰልጣኙ፤

“ምን ያረግልኛል!”

“ እግርህንና መቀመጫህን ያዳብረዋል”

“ እግሬን ከመቀመጫየ ነጥሎ እሚያዳብር ስፖርት የለም?”

“ የለም! “ አለኝ ኮስተር ብሎ” ተያያዥ ስለሆኑ አብረው ነው እሚዳብሩት! “

ስተክዝ እንዲህ ብሎ አጽናናኝ::

“ አትጨናነቅ! መቀመጫህን ወደ ነበረበት ለመመለስ በሚቀጥለው አመት ሌላ ስፖርት እንሰራለን”

እንቅስቃሴን ስጨርስ ገላየን ታጠብሁ፤ ከዛ ብብቴን ወይባ ታጠንኩ፤ በአስር አመት ወደ ወጣትነቴ የተመለስሁ መሰለኝ! የሸሚዜን ሶስት ቁልፎች ፈታሁና ሩብ ደረቴን ለብርድና ለህብረተሰቡ እይታ አጋለጥኩት፤ ከ” ሮዛ” የሞዴል ማሰልጠኛ ለሻይ እረፍት የወጡ ኮረዶች “ He is out of my league በሚል አይነት እሚያዩኝ መሰለኝ፤ በዚህ ቅርጽ ላይ ትንሽ ዝነጣ ልጨምርበት ብየ፥ እግሬን በስታይል ፥ ጎተት አያደረግሁ መራመድ ጀመርሁ፤

ግቢያችን በር ላይ ስደርስ ፥ ዘበኛው በአዘኔታ ከንፈራቸውን አስጩኸው መጠጡና ፥

“ ሪህ ነው ልጄ?”

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19