Get Mystery Box with random crypto!

'አለሽ ወይ' በዕውቀቱ ስዩም አለሽ ወይ አለሽ ወይ አለሽ ወይ በጤና ይመስገን ደመና፤ በገበ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

"አለሽ ወይ"

በዕውቀቱ ስዩም

አለሽ ወይ አለሽ ወይ
አለሽ ወይ በጤና
ይመስገን ደመና፤

በገበሬው አጥንት፣ መሬቴን እያረስኩ
እንጀራ ሲጠፋ፣ ገበሬ እየጎረስኩ።
አለሁኝ በደህና
ይመስገን ደመና፤

ሰው ሲያፈርስ እያየሁ ሰው ሆኖ ቡልዶዘር
አንዱ ጭቃ ነገድ ሌላው የብረት ዘር
በፈረሰ ሰው ላይ በቆመ ሰገነት
ሲዖል አናቱ ላይ በታነፀ ገነት
ይኽን ኑሮ ብለው ጥቂቶች ሲኖሩ
ያለምንም ፀፀት ያለምንም ሃፍረት
ይህንን እያየሁ በታላቅ ፅሞና
አለሁኝ በደህና
ይመስገን ዳመና፤

በምቾት መዲና የምንዱባን ትዝብት
እንደ ሀሩር ልፎኝ
በጠዳው ጎዳና
ለማኝ ብላቴና
እንደ ጉቶ አናቅፎኝ
ሃፍረት እንደ ዝናር ከፊት ከኋላ ኣቅፎኝ
ልክ እንደ ገባሮች ለመኖር እያቀድሁ
በጌቶች መሶብም እጀን እየሰደድሁ
አለሁኝ በደህና
ይመስገን ደመና፤

ወይ በሩን አሳዪን ወይ ጠቁሚን መላ
ማዕበል ሲቃረብ ያመልጣል ሺመላ
በነፋስ ገፅ ፊት ይሸሻል ደመና
የኔ አዚም ያለበት ያ’ገሬ ሰው ግና
በስጋ ደም አጥንት የተሰራ አይመስል
እንደ ኮንሶ ሃውልት የመቃብር ምስል
አይሸሽ አያባርር ወይ አይተነፍስ ቃል
እንጨት ሆኖ ቆሞ ሰደድ ይጠብቃል፤

ይህንን እያየሁ
ሁኘ በጥሞና
አለሁኝ በደህና
ይመስገን ደመና፤

አንቺ ግን አለሽ ወይ እኔ አለሁ በደህና
አለሁ ግርምት ወሮኝ
ምላሱን በምላጭ እንደተሰለበ
ምናገረው ኖሮኝ
የምለው ቸግሮኝ።


ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19