Get Mystery Box with random crypto!

#ማራናታ ( ጌታ ሆይ ቶሎ ና ) Repost . . ነፍሴን ሳላሽራት ከሀጥያት ዕድፍ፣ በስምህ ሳል | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

#ማራናታ
( ጌታ ሆይ ቶሎ ና )
Repost
.
.
ነፍሴን ሳላሽራት ከሀጥያት ዕድፍ፣
በስምህ ሳልዳኘው የስጋዬን ጉድፍ።
እንደ ጷግሜ ዝናብ፤
እንደ ውሃ ደራሽ አልፎ የቀን ስንኩል፣
ስናፍቀው የነበር ከተስፋ ቃል እኩል።
ደርሶ ሳያበቃኝ ለሀገሬን ትንሳኤ፣
ሳልወጣ አደባባይ ሳልከርመው ሱባኤ።
ጌታ ሆይ አትምጣ !!
ጌታ ሆይ አትምጣ ትንሽ ጊዜ ሰጠኝ፣
ነፍሴም ልተጣጠብ ፍቅርህ ይለውጠኝ።
እባክህ ጌታ ሆይ.......
እኔ ስልጡን ባርያ እኔ ብኩን ልጅህ፣
አፈር ትቢያ አካሌን አቁሜው ከደጅህ።
በተማፅኖ እንባ በኩርማን በዓቴ፣
እስክትምረኝ ድረስ ይህ ነበር ፀሎቴ።
"እባክህ አትምጣ!!!"
.
.
አሁን ግን አምላኬ ፤
አሁን ግን ጌታ ሆይ አልልህም ማረኝ፣
መሰንበቴም ይፍረስ አልልም አኑረኝ።
በተቀጠቀጠ በቆጠለ አካል፣
በተነባበረ በሰው በድን መሃል፣
እንዴት ነው መፀለይ?፤
እንዴት ነው መማፀን ?!
እንደምን እንደምን እንዴት ልለማመን።?
አምባ ነፍስያችን ቤተ እምነት ነደዱ፣
አፀደ እግዜር ማሳ ተርታ ሆኗል መስጂዱ።
እንዴት ነው መፀለይ ፤?
መሻገሪያው ድልድይ፤
ሙሴ ያልነው መሪ መንገድ ላይ ትቶናል፣
ማን ቀብቶት እንጃ ወርዶ አዋርዶናል።
ሚስኪን ሀገሬ እንኳን፤
ከአለም ተነጥላ ላመነችው ጌታ፣
"ኤሎሄ"
"ኤሎሄ"
"ኤሎሄ" እንዳለች እጆቿን ዘርግታ።
ለልጆቿ ታምና ታፍራ እንዳልተመካች፣
በአብራኳ ክፋይ በጥፊ ተመታች።
( የሚያሳዝን እውነት )
.
.
እንደምን ልማፀን ?፤
እንዴት ልለማመን።?
የስጋ ፍላጎት ሰው ከመሆን ነግሷል፣
በልባችን መንበር ሰይጣን ቤት ቀልሷል።
መፀለይ ምንድነው፤
መንበርከክ ምንድነው።?
በገረረ ብረት በጦር በጎራዴ፣
በሳንጃ በጩቤ በሻገተ ጓንዴ።
የፈጠርከውን "ሰው" እንደ በግ አርደናል፣
እንደ እንጨት ረብርበን ፍጡር አንድደናል።
.
.
እናም ጌታችን ሆይ.....
እየደጋገምን ዝንት ብንበድልም፤
እፁብ ቤተ መቅደስ እልፍ ሰው ብንገድልም፤
ባለ ብዙ ምህረት ቸር አምላክ ነህና፣
አገኛለሁ ብለህ ቀናዒ ልቦና።
በእዝነት አስበህ ልትምረን ከመጣህ ፣
አትጠራጠረኝ፤
ድጋሚ መገረፍ መሰቀል ነው እጣህ።
ስለዚህ ጌታ ሆይ.....
እኛ ብኩን ህዝቦች፣
እኛ ብስቁል ህዝቦች፤
በ'ለት ኑረት መሃል በስጋ ህላዌ፣
ክፋት ምቀኝነት የከረመ ደዌ።
ጠፍሮ ተብትቦ እንዳወላገደን፣
'ባክህ ቶሎ ናና ጠራርገህ ውሰደን።
.
.
.
"በል ፀሎቴን ስማኝ፤
አንተ ታላቅ ንጉስ አንተ ታላቅ ጌታ፣
"እግዚኦ.. ዘላለም እግዚኦ.. ማራናታ።"
.
.
.
......የወንድምህ ህመም አንተን የማይሰማህ ከሆነ "ሰው" መሆንህን ተጠራጠር....

       ዓቢይ ( @abiye12 )

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19