Get Mystery Box with random crypto!

#Scam_Alert 'Fias 777' በሚል ስያሜ የኮሚሽን ስራ እሰራለሁ ብሎ ከሰዎች ብር እየ | Birhan Nega

#Scam_Alert

'Fias 777' በሚል ስያሜ የኮሚሽን ስራ እሰራለሁ ብሎ ከሰዎች ብር እየሰበሰበ የሚገኘው 'ድርጅት' ምንድን ነው?

ከሰሞኑ እጅግ በርካታ የሆኑ ተከታታዮቻችን Fias 777 በሚል ስያሜ የሚንቀሳቀሰው ድርጅት ምንነት እና ህጋዊነትን በተመለከተ ጥያቄዎች ሲደርሱን ነበር።

ድርጅቱ ራሱን "የኮሚሽን የሚሰራ የማስታወቂያ ድርጅት" ብሎ የሚጠራ ሲሆን "ከተለያዩ የሶሻል ሚዲያ ኔትዎርኮች ጋር እንሰራለን" ይላል። አክሎም "በቀን ውስጥ የተለያዩ ስራዎችን ለተመዘገቡ አባላቶቹ እንሰጣለን። ስራዎቹ እጅግ በጣም ቀላል ናቸው። ክሊክ ማድረግ ብቻ ነው። በዛ ቢባል 5 ደቂቃ ቢወስዱ ነው። አንድ አባል የሚሰጠው የስራ ብዛትና የሚያገኘው ብር እንደ ደረጃው ይለያያል። ደረጃዎቹ VIP-0, VIP-1, VIP-2, VIP-3, VIP-4, & VIP-5 ናቸው" ይላል።

እንደ ድርጅቱ አባባል ለምሳሌ በVIP 4 ደረጃ ላይ አንድ አባል 10,000 ብር ከፍሎ ደረጃ ይሰጠዋል። በቀን ክሊክ የሚያደርጋቸው 17 ስራዎችን ነው፣ ለአንዱ ስራ 18 ብር ይከፈለዋል። ይህም በቀን 306 ብር ወይም በወር 9,180 ብር ያገኛል" ይላል።

እንደ ድርጅቱ ገለፃ አሁን ላይ "በኢትዮጵያ ውስጥ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በሰፊው ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ፍቅር ያለው ሲሆን የተመዘገቡትም ቁጥር 2 ሚሊዮን ደርሷል" ይላል።

ይሁንና ድርጅቱ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ እንዳይንቀሳቀሱ እገዳ ተጥሎባቸው እንደነበሩት #QuestNet እና #Tiens ያሉ የፒራሚድ ስሌትን መሰረት ያደረጉ ድርጅቶች ስራውን እንደሚያከናውን ማየት ችለናል። ይህም ብዙ ሰዎችን በስር በማስገባት የሚከናወን ሲሆን ቀድመው የገቡ ሰዎች ገንዘብ ሲያገኙ በርካቶች ግን ተጭበርብረው ይቀራሉ።

ለድርጅቱ ክፍያዎች የሚፈፀሙት በአቢሲንያ ባንክ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካኝነት እንደሆነ ኢትዮጵያ ቼክ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።

በዚህ ዙርያ ያናገርነው አንድ የድርጅቱ ተጠቃሚ "ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ምዝገባም ሆነ ቢሮ የለውም፣ ባለቤቶቹንም አናውቃቸውም" ያለ ሲሆን ከሰሞኑ ብዙ #ቅሬታዎች መነሳት እንደጀመሩ ይገልፃል። "ጥያቄ ስንጠይቃቸው ከ Fias ትባረራላችሁ ይሉናል፣ ግልፅነት የለበትም" ያለ ሲሆን ስራውን ግን እንደገፋበት ይገልፃል።

ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ምዝገባ እንዳካሄደ ቢገልፅም ይህ ትክክል እንዳልሆነ ከንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባ ፅ/ቤት ማጣራት ችለናል።

ሌላው ድርጅቱ የሚሰራው ስራ ምን እንደሆነ በኢትዮጵያ ቼክ የተጠየቀ አንድ የድርጅቱ ተወካይ ነኝ የሚል ግለሰብ "ሰዎች የፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ቲክቶክ እና ዩትዩብ ምስሎችን ሲጫኑ ተመልካች ይበዛላቸዋል፣ ለዚህም ከነፌስቡክ ክፍያ እናገኛለን፣ ከነሱ ጋር አብረን እንሰራለን" ብሏል። ነገር ግን ወደነዚህ የማህበራዊ ሚድያ የሚወስድ ሊንክ እንደሌለ መመልከት ችለናል።

በዚህ ዙርያ ከፌስቡክ ጋር አለን ያሉትን ስምምነት እንዲያሳይ የተጠየቀው የድርጅቱ ተወካይ ነኝ ያለው ግለሰብ "የእኔ እጅ የለበትም፣ ውጭ ሀገር ያሉት ሰዎች ጋር ነው" ብሎ መልስ ሰጥቷል።

በተጨማሪም አጭበርባሪ ድረ-ገፆችን የሚከታተሉት Scam Advisor እና Scam Detector ገፆቹ አጭበርባሪ እንደሚመስሉ ያወጧቸው ሪፖርቶች ይጠቁማሉ:

-https://www.scamadviser.com/check-website/fias777.com

-https://www.scam-detector.com/validator/fias777-com-review/

እስካሁን በርካታ ሰዎች ከጥቂት መቶ ብሮች እስከ አስር ሺህ ብር ክፍያ ለድርጅቱ በሁለቱ ባንኮች አማካኝነት ፈፅመዋል። ይሁንና ከእንዲህ አይነት የማጭበርበርያ ስልቶች ህብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ እንመክራለን።

Eth Checkiopia

#Share
@ethio_techs @ethio_techs