Get Mystery Box with random crypto!

የየካቲት 4 ቀን፣ 2013 ዓ.ም. የዓለም ዜና *ሒውማን ራይትስ ዎች የተሰኘው ዓለም አቀፍ የሰብ | DW Amharic

የየካቲት 4 ቀን፣ 2013 ዓ.ም. የዓለም ዜና

*ሒውማን ራይትስ ዎች የተሰኘው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት፦ በትግራይ ገጠራማ አካባቢዎች ከሦስት ወር በፊት ከጦርነት ሕግ ውጪ የሆኑ የመድፍ ጥቃቶች ተፈጽመው እንደነበር ዛሬ ገለጠ።ድርጅቱ በተዋጊ ኃይላት ተፈጸሙ የተባሉትን ጥሰቶች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲያጣራ ጠይቋል። ዓለም አቀፍ ድርጅቱ፦ ሱዳን ውስጥ የሚገኙ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ 37 ምስክሮችን በስልክ በማነጋገር ባለፉት ሁለት ወራት አሰባሰብኩት ባለው መረጃ የኢትዮጵያ ጦር ያለ ጥንቃቄ ገጠራማ ቦታዎችን ደብድቧል ብሏል። ሕወሓት ከመቀሌ ወደ ባህርዳር እና ኤርትራ መዲና አስመራ ሮኬቶችን ሲያስወነጭፍ እንደነበር ግን የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ አልዘገበም። የኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦር መኮንንኖች በውጊያው ወቅት የኢትዮጵያ ጦር ስነ ምግባርን የተከተለ ነበር፤ በውጊያ ወቅት የሚከሰተው ተጓዳኝ ጉዳትም አነስተኛ ነው ማለታቸውን ግን ጠቅሷል። የዓለም አቀፍ ድርጅቱ የአፍሪቃ ቀንድ ኃላፊ ላቲፋ ባደር፦ ጥንቃቄ ያልነበረው ባሉት ጥቃት «ሰላማዊ ሰዎች እና ንብረት» መጎዳታቸውንም ገልጠዋል። በያኔው ጥቃት ቢያንስ 83 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው እና 300 መቁሰላቸውንም መግለጫው ጠቅሷል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፦ «የኢትዮጵያ ትግራይ ክልል፡ የመሰረታዊ ልማት፣ የማኅበራዊ እና የአስተዳደራዊ አገልግሎቶችን በአፋጣኝ የመመለሱ ተግባር ልዩ ትኩረት ይሻል» ብሏል። ኮሚሽኑ ገና በአካል ተገኝቶ ክትትል ለማድረግ እንዳልቻለ በገለጠባቸው በርካታ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ስላለው ሁኔታም ገልጧል። «የሰው ሕይወት ማለፉን፣ የአካላዊ እና ሥነልቦናዊ ጉዳት መድረሱን፣ ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ ዘረፋ እና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ስለመፈጸማቸው መረጃዎች» ደርሰውኛል ሲልም አክሏል።

*የአፋር ክልላዊ መንግሰት በትግራይ ክልል ለሚገኙ ርዳታ ፈላጊዎች ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት እለታዊ ድጋፍ ማድረጉን ዐስታወቀ።ሌሎች ክልሎችም በትግራይ ክልል ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ የአፋር ክልላዊ መንግስት ጥሪ አድርጓል። የአፋር ክልል መንግስት የአደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ዛሬ ለዶይቼ ቬለ (DW)እንደገለፁት ክልሉ ድጋፉን የተለያዩ የመባእልት ድጋፍ አድርጓል። «የተደረገው ድጋፍ የተለያዩ የምግብ አይነቶች ናቸው። 1500ኩንታል ሩዝ አለበት፤ 900 ኩንታል ነጭ ዱቄት፤ እንዲሁም ፓስታ፣ ማካሮኒም አለ። ጨው ደግሞ 200 ኩንታል አለ። በአጠቃላይ 2700 ኩንታል ነው። በብር ሲተመን ከ9 ሚሊዮን በላይ የሚገመት ርዳታ ነው የተደረገው።» አቶ መሐመድ ክልላቸው ለተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋልጦ እንደነበር በማስታወስ ዛሬ ያደረጉት ርዳታም ተርፏቸው ሳይሆን ወገንን ለማዳን የተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። «እኛ ያቀረብነው በቂ ነው ማለት አይቻልም። እኛ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆነን ነው። እኛም የጎርፍ አደጋ፣ የአንበጣ እና ሌሎች ተዛማጅ አደጋዎች ነበሩብን።»

*በትግራይ ክልል አንዳንዶቹ 4 ሚሊዮን 500 ሺህ ህዝብ የምግብ ርዳታ እንደሚያስፈልገዉ የተለያዩ ወገኖች አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የተባለው ቁጥር በመረጃ ያልተደገፈ መሆኑን በመግለጥ በክልሉ ያለው የተረጂ ቁጥር ከ2 ሚሊዮን 500 ሺህ እንደማይበልጥ በተደጋጋሚ አመልክቷል። የባህር ዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን ከትግራይ ክልል ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት ባለስልጣናቱ ስልክ ባለማንሳታቸዉ አልተሳካም።
*የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር፦«የትግራይ ክልል 80 በመቶው ከርዳታ አቅርቦት ተቋርጧል» ብሏል በማለት የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ) ያሰራጨዉን ዜና ማሕበሩ የተዛባ ነው በማለት ማዘኑን ገለጠ። የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር፦ እስካሁን 400,000 ተረጂዎችን ማለትም ከአጠቃላዩ 20 በመቶውን መድረስ መቻሉን ገልጧል። ማኅበሩ ዛሬ ለሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ አውታሮች በሰጠው ጋጤጣዊ መግለጫ በትግራይ፣ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ተጨማሪ ሰዎች ርዳታ እንዲያገኙ ለማድረግ እየጣረ መሆኑን ዐስታውቋል። በዛሬው መግለጫ፦ የቀይ መስቀል ማሕበር ዓለም አቀፍ ፕሬዚደንት ፍራንሴስኮ ሮካ እና የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ፕሬዚደንት አቶ አበራ ቶላ ከአዲስ አበባ እና ከጄኔቫ በኢንተርኔት መገናኘታቸውንም ተገልጧል። አቶ አበራ ቶላ፦ በእንግሊዝኛ የተናገሩት እና በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የተሰራጨው አጠር ያለ ቪዲዮ «በአሁኑ ወቅት 80 በመቶው ትግራይ መድረስ የማይቻል ነው» ይላል። የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ቅሬታ ያቀረበበት የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዜናን በመጥቀስ፦ «ፕሬዚደንታችን በመግለጫቸው ወቅት መልከዓ-ምድራዊ ቦታዎችን አልጠቀሱም» ብሏል። ማኅበሩ ትግራይ ውስጥ ርዳታ ወደሚያስፈልጋቸው ዜጎች ለመድረስ «መቼም ተከልክሎ ዐያውቅም» ሲል በመግለጫው አክሏል። አያይዞም የማኅበሩ ፕሬዚደንት «ትግራይ ውስጥ 80 በመቶ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ለመድረስ» በአሁኑ ወቅት ስላጋጠመው የአቅም እና የአቅርቦት እጥረት ነው የገለጡት ሲልም አስተባብሏል።

*ጀርመን የኮሮና ተሐዋሲ ሥርጭኅን ለመግታት የጣለችውን የእንቅስቃሴ ገደብ ለተጨማሪ ሦስት ሳምንታት አራዘመች። የሀገሪቱ መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የተሐዋሲውን «አደገኘነት» በመጥቀስ «ብርቱ ጥንቃቄ» ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከክፍላተ ሃገራት መሪዎች ጋር ቀደም ሲል ባደረጉት ውይይት የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ የሚያበቃው የፊታችን እሁድ ነበር። ሆኖም እንደ ብሪታንያ እና ደቡብ አፍሪቃ ልውጥ የኮሮና ተሐዋሲ ጀርመን ውስጥ በመከሰቱም የሚያደርሰው ጉዳት ስለማይታወቅ ገደቡ መራዘም እንዳለበት ትናንት ማታ ተስማምተዋል። የኮሮና ተሐዋሲ ሥርጭት ግን ጀርመን ውስጥ በተወሰደው ጠንካራ ርምጃ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ተገልጧል። በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ የሆነው ምን ያህል ፍጥነት እና የጉዳት መጠን እንዳለው ያልታወቀው ልውጡ ተሐዋሲ ነው። ከ18 ቀናት በኋላ መዋዕለ ህጻናት እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚከፈቱ፤ የጸጉር ቤቶችም በጥንቃቁ ሥራ መጀመር እንደሚችሉ ተገልጧል። ትምህርት ቤቶች መች ይጀምሩ ለሚለው ግን 16ቱ ክፍላተ ሃገራት መሪዎች በየግላቸው እንዲወስኑ ተብሏል። የጀርመን መሪዎች የእንቅስቃሴ ገደቡን ስለማንሳት ወይንም ስለማላላት፣ አለያም ስለማራዘም ለመወሰን የዛሬ ሦስት ሳምንት ቀጠሮ ይዘዋል።