Get Mystery Box with random crypto!

የቱርኩ ፕሬዚዳንት ራስብ ጠይብ ኤርዶሃን ዩናይትድ ስቴትስ በኢራቅ የሚገኙ እና «አሸባሪ » ላሏቸው | DW Amharic

የቱርኩ ፕሬዚዳንት ራስብ ጠይብ ኤርዶሃን ዩናይትድ ስቴትስ በኢራቅ የሚገኙ እና «አሸባሪ » ላሏቸው የኩርዲስታን ሚሊሻዎች ትወግናለች ሲሉ ከሰሱ። ፕሬዚዳንቱ ክሱን ያሰሙት የኩርዲስታን ሠራተኞች ፓርቲ በእንግሊዘኛ ምህጻሩ ፒኬኬ በሰሜናዊ ኢራቅ አብዛኞቹ ወታደሮች የሆኑ 13 ቱርኮችን ገድለዋል የሚል ስሞታ ከቀረበባቸው በኋላ ነው። የኩርዲስታን ሚሊሻዎች ከደቡባዊ ምሥራቅ ቱርክ አግተው የወሰዷቸውን አብዛኞቹ የመንግሥት ወታደሮች እና የፖሊስ መኮንኖችን በሰሜናዊ ኢራቅ ዋሻዎች ውስጥ ሸሽገዋቸው እንደነበር የፈረንሳይ ዜና ምንጭ ዘግቧል። ፒኬኬ እጎአ ከ1984 ዓ/ም ጀምሮ በቱርክ መንግሥት ላይ በጀመረው አመጽ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ ይታመናል። ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የቱርክ አጋር የሆኑት የተቀሩት ምዕራባውያን ፒኬኬን በአሸባሪነት ፈርጀው እንደነበር ዘገባው አስታውሷል። ነገር ግን ዩናይትድ ስቴትስ በተናጠል በሶርያ የሚገኙ ሌሎች ኩርዳውያን ሚሊሻዎችን ስትደግፍ መቆየቷ ቱርክን አላስደሰተም። ቱርክ 13ቱን ታጋቾች ለማስለቀቅ በዚህ ወር በሰሜናዊ ኢራቅ ወታደራዊ ዘመቻ አካሂዳ ነበር። ባይሳካም ቅሉ። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ትናንት እሁድ ባወጣው መግለጫ «በቱርካውያን ላይ የተፈጸመው ግድያ ያሳዝናል፤ ነገር ግን ስለዘገባው ትክክለኛነት ተጨማሪ ማረጋገጫ ያስፈልገኛል» ብላለች። ነገር ግን የኩርዲስታን ኃይሎች ግድያውን መፈጸማቸው ከተረጋገጠ ዩናይትድ ስቴትስ አጥብቃ እንደምትኮንነው ዘገባው አያይዞ አመልክቷል።