Get Mystery Box with random crypto!

እስራኤል የኮሮና ስርጭትን ለመግታት ዘግታው የነበረውን ድንበር እና የዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ጣብ | DW Amharic

እስራኤል የኮሮና ስርጭትን ለመግታት ዘግታው የነበረውን ድንበር እና የዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ጣብያ ለተጨማሪ 14 ቀናት በዚሁ እንደምታራዝም አስታወቀች። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እና የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ይፋ ባደረጉት የጋራ መግለጫ ጥብቅ የዝውውር ሕጉ « በአስቸኳይ ምክንያት» እስከ የካቲት 27 ድረስ ይዘልቃል። የኮሮና ስርጭትን ለመግታት በሚል እስራኤል ከአለፈው ጥር 16 ጀምሮ የዓለም አቀፍ በረራዎችን ማስተናገድ ማቋረጧ ይታወሳል። ከዚህ ቀደም ሲል እስራኤል ከዮርዳኖስ እና ከግብፅ ጋር የሚያገናኛትን ድንበር ዘግታለች። እንድያም ሆኖ ከኢትዮጵያ፤ ከፈረንሳይ ከሩስያ ከዩክሬይን እና ከደቡብ አፍሪቃ የሚገቡ ይሁዶችን ለማጓጓዝ ስድስት የተለየ የዓለም አቀፍ በረራ መኖሩን የእስራኤል የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል። ወደ እስራኤል የሚጓዙት እነዚህ ዜጎች እስራኤል እንደገቡ የኮሮና ስርጭትን ለመግታት ወደ ተዘጋጀላቸው የተለየ ቦታ እንዲያርፉ እንደሚደረግ የእስራኤል የስደተኞች ጉዳይ መሥርያ ቤት አስታውቋል። የኮሮና ስርጭትን ለመግታት ከፍተኛ ጥረት በሚደረግበት በአሁኑ ወቅት በእስራኤል በቀን በአማካኝ 4000 በኮቪድ 19 የሚያዙ ሰዎች መኖራቸው ተመዝግቧል። ይሁንና ይህ ቁጥር ከጥር ወር መጀመርያ ጋር ሲነፃፀር በ4000 የቀነሰ ነዉ። እስራኤል ውስጥ ባለፈው ጥር ወር በቀን 8000 ሰዎች በኮቪድ ይያዙ እንደነበር ተመዝግቧል። እስራኤል ውስጥ የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭትን ለመግታት ካለፈው ታኅሣስ ወር ጀምሮ የወጣው ጥብቅ የዝውውር ሕግ ለአራተኛ ጊዜ መራዘሙ ተዘግቧል። እንደ እስራኤል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ 741 ሺህ ሰዎች በኮሮና ተይዘዋል፤ 5,501 ሰዎች ደግሞ የኮሮና ተህዋሲ ባስከተለባቸዉ ህመም ህይወታቸውን አጥተዋል።