Get Mystery Box with random crypto!

የዐርብ፤ ሰኔ 2 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የዓለም ዜና አርዕስተ ዜና *ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 61 የ | DW Amharic

የዐርብ፤ ሰኔ 2 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የዓለም ዜና
አርዕስተ ዜና

*ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 61 የፖለቲካ ፓርቲዎች በአባልነት ያሰባሰበው «የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት» መንግሥት ሀገርን ከከፋ ቀውስ እና ብጥብጥ እንዲታደግ ጠየቀ ።

*ለሁለተኛ የፕሬዚደንትነት ሥልጣን የሚወዳደሩት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በልደታቸው ዋዜማ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው። ማክሰኞ ሚያሚ በሚገኝ ፍርድ ቤት ሰባት ክሶች ይጠብቋቸዋል።

*የሱዳን ተፋላሚዎች ለ24 ሰአታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ዛሬ ማድረጋቸው ተገለጠ ። የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከቅዳሜ ንጋት ይጀምራል ተብሏል ።

ዜናው በዝርዝር

*የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ብልጽግናን ጨምሮ 61 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት ያሰባሰበው «የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት» ዛሬ አዲስ አበባ ኢሊሌ ሆቴል ውስጥ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፦ መንግሥት ሀገርን ከከፋ ቀውስ እና ብጥብጥ እንዲታደግ ጠየቀ ። የጋራ ምክር ቤቱ በከፍተኛ ደረጃ እየተሸረሸረ ነው ያለውን የፖለቲካ ምህዳር እንዲያሰፋ እና የዜጎችን ሕይወት እና መብት እንዲጠብቅም አሳስቧል ። ግጭት እና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ዜጎችን ለሞት፣ ለአካል መጉደል፣ መፈናቀል እና የሥነ ልቦና ስብራት እየዳረጉ ነው ያለው የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ በትግራይ ክልል አንፃራዊ ለውጥ መታየቱን ጠቅሷል ። በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በጋምቤላ ክልሎች ያለው የሰላም ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ የፀጥታ እና የደህንነት ተቋማት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ገለልተኝነት ሕግና ሥርዓትን እንዲያስከብሩ ጠይቋል። ተጨማሪ ዘገባ በዜና መጽሄታችን ይኖረናል ።

*በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን በሕዝብ ማጓጓዣ አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሁለት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ አራት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገለጠ ። በጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ አቅራቢያ «በዳ መጋጤ» በተባለ ስፍራ በሕዝብ ተሽከርካሪው ላይ የተኩስ እሩምታ የተከፈተው ማክሰኞ (ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም እኩለ ቀን 7፡00 ገደማ) ነው ተብሏል ። ከአደጋው የተረፉ የዐይን እማኞች እና የመንግስት ባለስልጣናት ጥቃቱን ያደረሰው መንግሥት «ሸኔ» በሚል በሽብርተኝነት የፈረጀው እና ራሱን «የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት» ሲል የሚጠራው ሸማቂ ቡድን ነው ብለዋል ። በታጣቂ ቡድኑ በኩል ግን ስለዚህ ጥቃት የተሰጠ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልተሰማም ። ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የዐይን እማኝ ይህን ብለዋል ። «አደጋው የገጠመን በባቱ ከተማ የእንስሳት ልማት ፖኬጅ ስልጠና ለአራት ቀናት ያህል ወስደን ወደ ቤታችን እተመለስን በነበርንበት ነው ፡፡ እየተጓዝን የነበረው በሕዝብ ትራንስፖርት ነበር ፡፡ ድንገት ነው የታጠቁ አካላት ተኩስ ከፍተውብን ስንጓዝበት የነበረውም መኪና ከመንገድ ወጥቶ ጫካ ውስጥ የገባው፡፡ በተከፈተው የተኩስ እሩምታ ሁለት ሰዎች ወዲያው ሲሞቱ አራት ሰዎች ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሷል ፡፡ ድንገት የተኩስ እሩምታ ሲከፈትብን ብቻ ነው ያየነው ።»
የምዕራብ ጉጂ ዞን ፀጥታ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ገዳ ጎዳና በበኩላቸው ይህ ጥቃት ከመፈጸሙ ከደቂቃዎች አስቀድሞ በመንግስት ጦር እና «ኦነግ ሸኔ» ባሏቸው ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ገልጠዋል ።
«ያው ጠላት ሸማቂ እንደመሆኑ አድፍጦ አደጋ የማድረስ ስልት ነው የሚጠቀመው ። ከ300-400 ሜትር ርቀት ውስጥ የመንግስት ታጣቂዎች በቅርቡ ነበሩ ። አደጋው በተፈጠረበ ት በዚህ የበዳ መጋጤ ደን ውስጥ ታጣቂዎች እና የመንግስት ሰራዊት መካከል ተኩስ ነበር ። በዚህ ደን ውስጥ የመንግስት ጦርም ሆነ የሸማቂ ቡድኑ ጦር አለ ። አሁን ችግሩ አልፎ አልፎ የሚያጋጥመን ነው እንጂ መንግስት መንገዱን ተቆጣጥሮ ጥበቃ እያደረገ ነው ።»
በቅርቡ በመንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል በታንዛንያ የተጀመረው የሰላም ድርድር ያለ ተጨባጭ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች በመንግስት እና ሸማቂ ቡድኑ መካከል ግጭት ተባብሷል መባሉን የአዲስ አበባ ዘጋቢችን ሥዩም ጌቱ የላከልን ዜና ይጠቁማል።

*ባለፈው ዓመት ጥቅምት 18 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ከምስራቅ ወለጋ ነቀምቴ ከተማ ወደ ሳሲጋ ወረዳ ሲጓዙ በታጣቂዎች የታገቱ 28 የመንግስት ሠራተኞች ከዓመት ከመንፈቅ በኋላም ደብዛቸው ጠፍቶ መቅረቱን የታጋቾቹ ቤተሰቦች ለዶቼቬለ ተናገሩ ። የአራት ልጆት እናት መሆናቸውን እና ባለፈው ዓመት ባለቤታቸው እንደታገቱባቸው የተናገሩ አንዲት የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ ከወረዳ እስከ ዞን አስተዳደር አቤት ቢሉም እስካሁን ምንም መፍትሄ አለማግኘታቸውን ገልጠዋል ። ስለ እገታውም ቀጣዩን ብለዋል።
«ጥቅምት 18 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ለሥራ በጠዋት እየሄዱ ነበር ። ከባለቤተ ጋር የሄዱ ሌሎች ሰዎች 3 ሰዓት አካባቢ ተመለሱ ። በመንገድ ላይ የታጠቁ ሰዎች የመንገሥት ሠራተኞችን ለይተው ለይተው ማስቀረታቸውን ሌሎችን ደግሞ ወደቤታቹ ሂዱ ብለው እንደመለሷቸው ነገሩን ። በዕለቱ ነው እንግዲህ ታግተው የተወሰዱ ስልክም አልደወሉም በዛው ነው የቀሩት ። ምንም የፖለቲካ ተሳትፎ ያልነበረው የግብርና ባለሞያ ነበር ። አራት ልጆች አሉን አሁን ለፍተኛ ችግር ተጋልጠናል ።»
አንድ የሐይማኖት አባትም ባለቤታቸው ከነቀምቴ ተነስተው ወደ ሳሲጋ ወረዳ እየሄዱ ባሉበት ሰዓት አዳሚ በምትባል ስፍራ መታፈናቸውን በወቅቱ ከእገታ ከተረፉ ሰዎች መስማታቸውን ተናግረዋል ። ሆኖም እስከ ዛሬ ድረስ የት እዳሉ ዐለመታወቁን መረጃውም ከመገናኛ ብዙኃን ዘንድ ሳይደርስ መቆየቱን አክለዋል ። በምስራቅ ወለጋ ዞን የሳሲጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓለማየሁ ኤጄታ 28ቱ የመንግሥት ሠራተኞች መንግስት «ሸኔ» በሚላቸውና ራሳቸውን «የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊ»ት ብለው በሚጠሩ ታጣቂዎች መታገታቸውን ተናግረዋል ። ስለ እገታው ከታጣቂ ቡድኑ በኩል የተሰጠ ማብራሪያ አለመኖሩን የአሶሳ ወኪላችን ነጋሣ ደሳለኝ ዘግቧል ።