Get Mystery Box with random crypto!

*የሱዳንን ጦርነት በመሸሽ በመተማ ዮሐንስ በኩል ብቻ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ከ42 ሺህ በላይ የ70 | DW Amharic

*የሱዳንን ጦርነት በመሸሽ በመተማ ዮሐንስ በኩል ብቻ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ከ42 ሺህ በላይ የ70 ሀገራት ዜጎች ወደ የአካባቢያቸው መሸኘታቸውን በአማራ ክልል የምዕራብ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት አስታወቀ ። የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ አበባው በዛብህ ከሱዳን ጦርነቱን ሸሽተው ኢትዮጵያ ለገቡ ሰዎች ስለሚደረገው ድጋፍ ቀጣዩን ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል ።
«የአደጋ ሥጋት ኮሚሽን ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ወደሚፈልጉበት ቦታ ያለክፍያ በነፃ ያጓጉዛል ። ቁጥራቸውን በተመለከተ ወደ ሰባት ሺህ ሊጠጋ ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል ስደተኛ መጠለያ ቦታ ሦስት ቦታዎች ላይ ለይተን አስረክበናል እንደመንግሥት ። አንደኛው መተማ ዮሐንስ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሰፊው ተሠርቶ እዚያ መጠለያ ነው ያሉት ። ሁለተኛው መጠለያ ሠፈር ኩመር ይባላል ። ወደ 56 ሔክታር የሚሆን ቦታ ነው፤ ከድንበር 70 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቀት ላይ ይገኛል ። ሦስተኛው አውላላ የሚባል ቦታ ነው ።»
አሁንም በየቀኑ ከሱዳን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ እንደሆነም ኃላፊው ተናግረዋል ሲል የባህር ዳር ወኪላችን ዓለምነው መኮንን ዘግቧል ። መሄጃ ለሌላቸው ስደተኞች አስፈላጊው የምግብና ሌሎች ድጋፎች በኢትዮጵያ መንግስትና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እገዛም እየተደረገ እንደሆነ ኃላፊው ገልጠዋል ። ሱዳን ውስጥ ሚያዝያ 2015 ዓ ም በጀነራል አብድልፈታህ አል ቡረሀን በሚመራው የሱዳን ጦር ሠራዊት እና ጀኔራል መሀመድ ሐምዳ ዳጋሎ ስር በሚገኘው የፈጥኖ ደራሽ ጦር መካከል ሚያዝያ 7 ቀ፣ 2015 ዓ.ም በተጀመረው ጦርነት ቢያንስ 883 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ። 3,800 የሚሆኑት ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደደረሰባቸው ተዘግቧል ።

*የሱዳን ተፋላሚዎች ለ24 ሰአታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ዛሬ ማድረጋቸው ተገለጠ ። የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከቅዳሜ ንጋት ይጀምራል ተብሏል ። ተፋላሚዎቹ ለአንድ ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት ስለማድረጋቸው በተወካዮቻቸው በኩል በጋራ በሰጡት መግለጫ መጠቀሱን የሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ዐሳውቋል ። «የሱዳን ጦር ሠራዊት እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) ከሰኔ 2 ቀን፤ ንጋቱ 12 ሰአት የሚጀምር ለ24 ሰአታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማምተዋል» በሚልም የጋራ መግለጫው ይነበባል ። በዋናነት በዩናይትድ ስቴትስ እና ሳዑዲ ዓረቢያ አሸማጋይነት ሱዳን ውስጥ ከዚህ ቀደም የተደረጉ በርካታ የተኩስ አቁም ስምምነቶች በተደጋጋሚ መክሸፋቸው የሚታወስ ነው ።

*ለሁለተኛ የፕሬዚደንትነት ሥልጣን የሚወዳደሩት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሰባት ክሶች እንደቀረበባቸው ተገለጸ ። ክሱ ከምሥጢራዊ የመንግስት ሠነዶች አያያዝ ጋር የተገናኘ ነው ተብሏል ። ዶናልድ ትራምፕ ግን ክሱን አጣጥለዋል ። «ሙሰኛው የባይደን አስተዳደር ክስ እንደቀረበብኝ ለጠበቃዬ ነግሯል ። ያው የተለመደ በሬ ወለደ ነው» ሲሉም ትሩዝ ሶሺያል በተባለው የማኅበራዊ የመገናኛ አውታራቸው ጽፈዋል ። ጠበቃቸው ጂም ትረስቲ ደምበኛቸው ላይ ሰባት ክሶች መቅረባቸውን ለሲኤንኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ መናገራቸውን የፈረንሣይ የዜና አገልግሎት (AFP) ዘግቧል ። ስለ ክሱ ጉዳይ ግን ዜናው በወጣበት ወቅት የሀገሪቱ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ያለው ነገር የለም ሲል አክሏል ። ዶናልድ ትራምፕ ከ77ኛ ልደታቸው አንድ ቀደም ብሎ ማክሰኞ ሚያሚ ውስጥ ወደሚገኝ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ጥሪ እንደደረሳቸውም ተናግረዋል ። የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ከተከሰሱባቸው ሰባት ጉዳዮች፦ መንግሥትን ስለመሰለል የሚያወሳውን ሕግ በመጣስ ሆን ብለው ሠነዶች እንዲያዙ አድርገዋል፤ የተሳሳቱ መግለጫዎችን ሰጥተዋል የሚሉት ይገኙበታል ተብሏል ።

የዓለም ዜናውን ሙሉ ዘገባ በድምፅ እዚህ https://p.dw.com/p/4SP25?maca=amh-RED-Telegram-dwcom ማድመጥ ይቻላል ። አስተያየት ለመስጠት፣ ጥቆማ ለማድረስ ይኽን ቦት ይጠቀሙ @dwamharicbot ማድመጥ ይቻላል።