Get Mystery Box with random crypto!

​‍ የጠፋው ሬሳ ምዕራፍ ሁለት ክፍል አስራ-ሶስት ደራሲ፡-የኔታ ፍቄ(ግጥም እና ፍቅር) ፡ .. | Emoji feelings🦋

​‍ የጠፋው ሬሳ
ምዕራፍ ሁለት
ክፍል አስራ-ሶስት

ደራሲ፡-የኔታ ፍቄ(ግጥም እና ፍቅር)


.......ወዳለሁበት ሲዋከቡ መጡ ግን የነበርኩበት አልጠበኳቸውም ከመቅፅበት አልጋው ስር ተመለስኩኝ፡፡ የቤቱ ድምድምት ላይ አይጥ ሲርመሰመስ አይተው ነው መሰል "እኚ የተረገሙ ትናንሽ ፍጥረታት" ስትል ሰማሗት ትንሿ ሴትዮ በብስጭት እርር ብላ፡፡

እግዜር እንድኖር ዕድሜን ከቅፅበት እየነጠቀ ከሞት እየተሻማ እየታደገኝ ነው፡፡ "ባላመሰግነውም ምስጉን ሆነው የነፍሴ ጠበቃ ይመስገን" አልኩኝ ለራሴ በድንጋጤ አካሌን ፈልቅቆ ሊወጣ ሚወራጨውን ልቤን ደግፌ፡፡

"አንገቷን በእጅህ ይዘህ ና" ስትል ሰማሗት ትንሿ ሴትዮ ነበረች፡፡ ምን አድርጌያት እንዲህ እንደጠላችኝ እንጃ፡፡ ዳሩ እኔም አልወዳትምና መጥላቷ ግድ አልሰጠኝም፡፡ በህይወት ከተረፍኩ በህይወት እንደማይኖሮ አሳባ እንደሆነ ማወቁ ከኔ የተሰወረ እውነት አልነበረም፡፡ ተከታትለው ሲወጡ ተሰማኝ፡፡ እኔም ጊዜ ሳላጠፋ ዳናዬን ዝግ አድርጌ ዱካቸውን ተከትዬ ወጣሁ፡፡

መንገዳቸው ከመንገዴ አልመግጠሙ እፎይታን ሰቶኛል፡፡ እኔ ወደግራ ስመለስ እነሱ ደግሞ ወደ ቀኝ ነበር የታጠፉት፡፡ አሁን በመሃከላችን ያለው ድንግዝ ለይተው እንዳያዩኝ እንደሚጋርዳቸው እርግጥ ነው፡፡ የሆነ ቦታ ላይ ሶስቱም ጀርባቸውን ለኔ ሰተው ቆመዋል፡፡

በውል ግን ምን እያደረጉ እንደነበር ማወቅ አይቻለኝም፡፡ ቤቱ ከቀድሞው ይልቅ ፈፅሞ ጨልሟልና፡፡ ከእርምጃዎች በሗላ ባርሳ ያለችበት ክፍል ደረስኩ፡፡ ጊዜ ሳላጠፋ የተሳረችበትን ለመበጠስ እንዲረዳኝ ጠረጴዛውን ስቤ እሱ ላይ ወጣሁ፡፡ እጇን በእጄ ይዤ በጥንቃቄ ቆረጥኩላት፡፡ አሁን ከባዱ የአንገቷ እስራት ነው፡፡

ሰንሰለተ አንገቷን ሰርስሮታል፡፡ ቀስ አድርጌ ግንባሯን ደገፍ አደረኩን ወደ ብረቱ አስጠጋሗት፡፡ በጣም ልዝብ ባለ ሁኔታ በማስተዋል ቀስ እያደረኩ መቁረጤን ተያያዝኩት፡፡ ትንሽ ስህተት ብሰራ አንገቷን መሬት ላይ ነው ማገኘው፡፡ ይህ ደግሞ ፈፅሞ መሆን የለበትም፡፡ ሰንሰለቱ አንገቷን ሶስት ጊዜ ዞሮ ተጠምጥሞባታል፡፡ ዙሩን ከመፍታት ይልቅ ሶስቱንም መቆራረጡ እንደሚሻል አውቃለሁ፡፡

ግን ደግሞ ፅልመቱ እየተገዳደረኝ ነው፡፡ የማደርገውን እለይ ዘንድ አልተቻለኝም፡፡ ቢሆንም ጀምሬዋለሁ፡፡ እጄ ፈፅሞ በደም ተጨማልቋል፡፡ ሰንሰለቱም እንደዛው በረጋ ደም ተሸፍኗል፡፡ የሰንሰለቱን ዙር የምለየው ጣቴን ወደ አንገቷ እስራት በስደድ ነው፡፡ ስለቱ እጅግ ቢሆንም ውፍረቱ ግን እምብዛም ነበርና ለመቁረጥ አያስቸግርም ከመማረቱ በቀር፡፡

ሁለቱን ቆርጫቸዋለሁ አንደኛው ግን አንገቷን ሰርስሯት ኖሮ ሊያዘኝ አልቻለም፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላወኩም፡፡ ግን ደግሞ ከጣቴ የቀጠነ አንዳች መያዣ ያስፈልገኛል፡፡ ለጊዜው መቁረቱን ተውኩትና ብዙ ስለቶች የተቀመጡበትን ጠረጴዛ ወደ መስኮቱ አስጠግቼ በሚዘልቀው ወገግታ ምፈልገውን መምረጥ ተያያዝኩት፡፡ መቀስ መሳይ ረዘም ያለ በቀዶ ጥገና ጊዜ የሰውን ቆዳ ለመያዝ የሚጠቀሙበትን መሳሪያ አገኘሁ፡፡

ግን አሁንም ቢሆን ፅልመቱ እሱን ለመጠቀም አዳጋች ነበር፡፡ የማለዳውን ብርሃን ታምኜ ለይደር ባዘገያት ከንጋት በፊት ሰንሰለቱ አንገቷን ሰርስሮ ይበጥሰዋል እናም አንዳች መላ መዘየድ አለብኝ፡፡ ክፍሉ ውስጥ ወዲህ ወዲያ ተንከላወስኩ፡፡ ትንሽ እንደቆየሁም አንዱ ጥጋት ላይ የጀርባ ቦርሳ አገኘሁ፡፡

እሱን ለመሸከም ሰውነቴ በድካም እና በስቃይ ተብሰክስኮ ነበርና እየጎተትኩ ወደ መስኮቱ ወሰድኩት፡፡ እንደምንም አንስቼ ጠረጴዛው ላይ ያለውን ዘረገፍኩት፡፡ የተለያዩ ልብሶች የሚቀባቡ ነገሮች ጫማዎች እንዲሁም የሚበላ ነገር በውስጡ ይዟል፡፡

ወዲያ ወዲህ እያመሰቃቀልኩ ለኔ ሚረባኝን ማሰሴን ተያያዝኩት፡፡ በድንገት የእጅ ባትሪ አገኘሁ፡፡ ደስታዬ ወደር አልነበረውም አበራሁት ይሰራል፡፡ መሳሪያዎቼን ይዤ ወደ ባርሳ ተጠጋሁ፡፡ ባትሪውን አፌ ውስጥ ከትቼ አንገቷ ላይ እያበራሁ ነፍስ ለማዳን ታተርኩኝ፡፡

ጥንቃቄ ከተሞላው ከደቂቃዎች ፈተና በሗላ ከሰንሰለቱ አንገቷን ነፃ አወጣሁት፡፡ ወገቧ ላይ ያለውን ቀበቶም ፈትቼ ቀስ ብዬ ከብረቱ አላቅቄ እግሬ ላይ ጋደም አደረኳት፡፡ ፀጉሯን እየደባበስኩ ትንሽ ከቆየሁ በሗላ ጠምቷት እንደው ብዬ አስቤ ውሃ ላጠጣት ወለሉ ላይ አስተኝቻት ተነሳሁ፡፡ ከቦርሳው ውስጥ ካገኘሁት ምግብ ጋር ውሃ ነበርና ቀስ አድርጌ አጠጣሗት፡፡ መዋጥ ለሷ ህመሟ ነበር በስቃይ ሁለት ጊዜ ተጎነጨች፡፡ ልብስ ደራረብኩላትና እግሬ ላይ አስተኛሗት እንድታርፍ በማሰብ፡፡

ከደቂቃዎች በሗላ በውጪ በኩል በመስኮቱጋ አንድ ሰው ውልብ ሲል ታየኝ፡፡ "በእግዚአብሔር ስም" አልኩኝ ድምፅ አውጥቼ፡፡ በድጋሜ በመስኮቱጋ ወደ መጣበት ተመለሰ ይህን ትዕይንቱን እየደጋገመ ነፍሴን አስጨነቃት፡፡ ይባስ ብሎ መስኮቱጋ ድንቅር ብሎ ቆመ፡፡

"ማነው" አልኩኝ ለራሴ ሳግ በተቀላቀለበት በሚሰባበር ቃል፡፡ ጥቁር ከመልበሱ በቀር ምንም አልታየኝም፡፡ ቀስ እያለ መስኮቱን ለመክፈት...ይቀጥላል


እንዲቀጥል አብሮነታችሁ አይለየን፡፡
ሀሳብ አስተያየት