🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

​‍ የጠፋው ሬሳ ምዕራፍ ሁለት ክፍል አስራ-ሁለት ደራሲ፡-የኔታ ፍቄ(ግጥም እና ፍቅር) ፡ .. | Emoji feelings🦋

​‍ የጠፋው ሬሳ
ምዕራፍ ሁለት
ክፍል አስራ-ሁለት

ደራሲ፡-የኔታ ፍቄ(ግጥም እና ፍቅር)


....እኔ ወዳለሁበት ክፍል እንደ ሰጋር ፈረስ የሚገሰግሱ የእግር ኮቴዎች ተሰሙኝ፡፡ እገባበት ጠፋኝ እሆነው ነገር ጨነቀኝ፡፡ በገዛ እጄ ወደሞቴ ገስግሼ እንደመጣሁ ነገሬ ሳያስፈልገኝ ለራሴው ገባኝ፡፡ ጊዜ ሳላባክን እሸሸግበት ጥጋት ፍለጋ ያዝኩ፡፡

ምንም አልታየኝም ያለሁበት ደርቄ ቀረሁ፡፡ ተስፋዬ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እኔን ጥሎኝ ኮበለለ፡፡ አሁን በድኔ ነው ከኔጋ ያለው፡፡ በቆምኩበት ሰከንዳት ተቆጠሩ፡፡ ህይወቴ በዚህ መልኩ ይቋጫል ብዬ አስቤም ይሁን ገምቼም አላውቅም፡፡ ያልጠበቅናቸው ሊሆኑ የጠበቅናቸው ሊቀሩ የህይወት ጉዞ ነውና ቢመርም መዋጥ ነው፡፡ የሰው ልጅ ራሱን የሚጎዳው በመጠበቅ ነው፡፡ የቀጠሩት ሲቀር ያበሳጫል፡፡ ባይቀጥሩትስ ብስጭቱ ቀረ ማለት አይደል፡፡

ነገን ዛሬ የሌለንን እንዲሞላልን ሙላታችንን ስንጠብቅ ሌላ ጎዶሎ ሲታደለን የልብ ስብራት ነው፡፡ ስለጠበቅን እንጂ ሳንጠብቀው ቢቀር ይህ ለኛ ምንድነው?፡፡ "ነገ ጥሩ ይሆናል ይላሉ" ባዮቹ "ቆይ ዛሬ ለምን ጥሩ አይሆንም? ነገ ከዛሬ የተለየ ለራሱ ጥሩነትን ማን ሰጠው? የጊዜ ጥሩ አለ ወይስ ባለጊዜው ጥሩ?" እያልኩ ከራሴ እሟገታለሁ የሞት ጊዜዬ እየተቃረበ ሰመመን ደግሞ ይዞኝ እየመጠቀ፡፡

የዛሬ መጥፎ የነገ ደግሞ ጥሩ የለም፡፡ ጥሩ ነገ አይመጣም ጥሩ ሁሌም አለ፡፡ ነገ መልካም አይደለም ዛሬንም ነገንም መልካም የሚያደርግ ፈጣሪ ዓለማትን በቃሉ ያጸናው እግዜር ብቻ ነው፡፡ ቀኑም አይደለም፣ምሽቱም አይደለም፣ንጋቱም አይደለም ዛሬ ወይ ነገም አይደሉም "እግዚአብሔር ብቻ ነው መልካም" ነገ መልካም ይሆናል ብለህ የቀኑን በጎነት አትጠብቅ "ለቀኑ የራሱ ክፋት ይበቃዋልና" ይላል ታላቁ መፅሐፍ ቅዱስ፡፡

"ከዚ የትም አትርቅም ትርቅም ዘንድ አቅሙ የላትም እንዳገኘሃት አናቷን ለሁለት ክፈለው" የሚል በሚያስገመግም ድምፅ ቁጣ ተቀላቅሎበት የተሰጠ ትዕዛዝ ከሀሳብ ሽልብታ ሰርቆ አወጣኝ፡፡ ድንዛዜዬ ቅቡጭ(ድንገት እልም) አለ፡፡

በነበርኩበት ለሰከንድ ሽራፌ አልቆምኩም ወደ ውስጠኛው ክፍል ሄጄ ከአልጋው ስር ራሴን ሸሸግሁ፡፡ ሶስቱም ተከታትለው ሲገቡ ይታወቀኛል፡፡ ቤቱ ውስጥ በጭንቀት ይሁን በእልህ ከወዲያ ወዲህ ይንጠራወዛሉ፡፡

የወለሉ ቅዝቃዜ ደና የጠገገ ቁስሌን ይመዘምዘው ጀምሯል፡፡ ድምፄን አውጥቼ ባማጥኩት ምነኛ ደስ ባለኝ ግና ቃሌ የሞት ጥሪን እንጂ ለስቃዬ ማስታገሻ አይሆነኝም፡፡ ያ ፀላኢ ሰይጣን አረመኔ አንደበቱ ቀንቶ የማይናገር አደዳ ቢጤ መሰለኝ ቃሎቹ በውል አይለዩም፡፡ ያቺ የከረከሰች አሮጊት የዚ ነብሰ በላ እናት ነች፡፡ ጭካኔውን እንኳ አይታ ያልረገመችው በመግደሉ ምትኮራ የሰው እርግማን ነች፡፡ አቅሙ ይኑረኝ እንጂ ሶስቱንም እገላቸዋለሁ፡፡

የውስጤ የተስፋ ማሾ ውስጤ መቀጣጠል ጀመረ፡፡ እንደምኖር አስቤ ለመግደል መመኘቴ ገረመኝ፡፡ እውነትም የእግዜር እንጂ የቀን መልካም የለውም፡፡

"እቺ ከረከንድ እራሪ ድውይ ትንሽ ሴትዮ መጥፊያዋ በመዳፌ" አልኩኝ ለበቀል ያቆበቆበ ልቤን ተማምኜ፡፡ "የኔ ነፍስ እዚ ክፍል ውስጥ የተከረቸመባት መናኛ ከየትም የበቀለች ወፍ ዘራሽ አስታዋሽ የሌላት የተረሳች መምጫዋ ማይታወቅ ፍጡር አይደለችም እንዲያውም ከስጋና ከደም ፈቃድ ውጪ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ወደ ምድር የመጣች እንጂ ታዲያ በማን ፍቃድ ከኔ ትለያለች እሱ ያበጃጀውን ያፈርስ ዘንድ ማንስ ይቻለዋል?" አልኩኝ ለራሴ በለሆሳስ፡፡

በደም እና በነፍስ የተገዛች ነፍስ የዋዛ አይደለችም፡፡ እኔ የኔ አይደለሁም ባለቤቴም ዝም ይል ዘንድ ተላላ ሰነፍ ቃሉም ከንቱ አይደለምና ያድነኛል፡፡ በማዳኑ ልክ ሳይሆን ያኔ በከፈለልኝ የፍቅሩ ልክ ተገዝቼለታለሁ፡፡ የመስቀሉ ውለታ ለደካማውና ለሚፈታተነኝ ስጋዬ መዳን የደቀቀ አይደለም ለዘላለማዊቷ እስትንፋሴ እንጂ፡፡

ወደ ጓዳው ዘልቀው አልገቡም ከሳሎን ሆነው ለነፍሰ በላው ነበልባል ጋዝ እየጨመሩ ውስጡ ያቀጣጥሉታል፡፡ ይመስለኛል እሱ ግን እኔን ለመበቀል ከመውተርተር ይልቅ ቅዛዜ ውስጥ ገብቷል፡፡ "ምን ሆነሃል አንድዬ" ከሚለው የትንሿ ሴትዮ ድምፅ ውስጥ ተረዳሁት፡፡ "እቺ ሴት ከዚህ ካመለጠች ሶስታችንም መጥፊያችን ነው ሚስጥራችን ገሃድ መዘርገፉ ነው ተነስ ፈልገህ ገላግላት" ትለዋለች ግሳፄ ባገዘፈው ቃሎቿ ትንሿ ሴትዮ፡፡

እስካሁን እናትየው አንዲትም ቃል አልተነፈሰችም፡፡ "ተዪው ልጄ ተዪው እስቲ እንደው እንደ ሰው ፍጡር ለሰው ማዘን ጀምሮ ይሆን እንዴ ለሱ ብዬ ከተሸሸኩበት ከዚ ከቀረና ክርፋት ከሞላው የነፍስ ዋይታ ካየለበት የሰው አጥንት ከተከሰከሰበት ስፍራ ወጥቼ ጎረቤቶቼ ጋር ልቀላቀል ይሆን እንዴ የማለዳ ፀሃይ እንኳን እኮ ናፈቀኝ ጀምበር ስታሸልብማ አይቻትም አላውቅ ይሄ እኮ ለኔ ህመም ነው ልጄ ሰውነት እየገዛው ከሆነ ብዬ እኮ ነው ተዪው አትቆጪው" አሉ እናትዬው ንግግራቸውን ሳግ እያቆራረጠ የእናትነት አንጀታቸው አላስችል ቢላቸው፡፡

እኔም ቢሆን አሳዝነውኛል ለልጃቸው ብለው የእተጋቱት ያለው የመከራ ፅዋ መራር ነው፡፡ ከንግግራቸው ይህ ሰው ከአመታት በፊት ሰውነት የነገሰበት ሰው ነበር ማለት ነው፡፡ "ታዲያ ምን ጉድ ምንስ ቅፅበት እንደዚ ወዳለ አረመኔነት ቀየረው?" ብዬ ጠየኩኝ መልስ የሚሰጠኝ እንዳለ ሁሉ፡፡

ቀስ ብዬ ከተደበኩበት አልጋ ስር ወጣሁ የሚሆኑትን እና የሚያረጉትን በስውር እመለከት ዘንድ፡፡ በዝግታ ወደ ሳሎኑ መውጫ ጋር ደርሼ መጋለጫው ገለጥ አድርጌ መመልከት ጀመርኩ፡፡ እሱ ከአንዱ ወንበር ላይ ዘርፈጥ ብሎ ቅዝታ ውስጥ ገብቶ ተክዟል እነሱ ግራና ቀኙ ቆመዋል ትንሿ ሴትዮ በእጇ የሆነ አጀንዳ የሚመስል ነገር ይዛለች ምን እደሆነ ለማየት ስንጠራራ ባላንሴን ሳትኩና ከበስተሗላዬ የተደረደሩ ድስቶች ላይ ወደኩ ቤቱ በአንዴ ተወክቦ ፀጥ አለ በዛው ቅፅበት ሶስቱም ወደኔ....ይቀጥላል

እንዲቀጥል አብሮነታችሁ አይለየን፡፡
#share #ሼር