2020-08-19 18:20:25
የክላውድ ኮምፕዩቲንግ ወሳኝ ሚና
*****************************በኮምፒውተር ኢንዳስትሪ ማርሽ ቀያሪ ሊባሉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች በየግዜው ይከሰታሉ። ክላውድ ኮምፕዩቲንግ ምናልባት ከነዚህ ተጠቃሽ ቴክኖሎጂ ውስጥ አንዱ ሊሆን ይችላል። ቃሉን በቀጥታ ወደ አማርኛ ከተረጎምነው ዳመና ላይ ማስላት ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና ይህን ዓይነት ትርጉም መስጠት ከቴክኖሎጂው መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብ ጋር ይበልጥ ስለማይጎዳኝ የእንግሊዘኛውን ስያሜ መጠቀም የተሻለ ነው።
ክላውድ ኮምፒዩቲንግ በአጭሩ ሲገለጽ የኮምፒውተር አገልግሎቶች ማለትም ሰርቨሮች፣ የውሂብ (data) ማጠራቀምያዎች፣ አውታር መረቦች፣ ሶፍትዌሮች እና ሌሎች አገልግሎቶችን ኢንተርኔት (ክላውድ) ተጠቅሞ የሚያቀርብልን ቴክኖሎጂ ነው። ይህ ማለት ውሂብ ወይም ዳታ የምናስቀምጠው በኮምፒተራችን ሳይሆን፤ ሌሎች ድርጅቶች በሚቆጣጠሩት ኮምፒውተር ነው ማለት ነው። ያስቀመጥነውን ውሂብ ማግኘት ስንፈልግ፣ ኢንተርኔትን ተጠቅመን ወደ የግላችን ኮምፒውተር መገልበጥ ወይም እዛው ክላውድ ላይ እያለ በማሰሻ (browser) ከፍተን ማየት እንችላለን። ይሁንና ክላውድ ኮምፒዩቲንግ ውሂብ ማከማቻ ጎተራዎች ብቻ አይደለም በአገልግሎት መልክ የሚያቀርብልን፤ ማንኛውም ኮምፒውተራችን ላይ ማድረግ የምንችለውን ተግባር በተሻለ ፍጥነት እና ዋጋ ማከናወን የሚይስችለን ቴክኖሎጂ ነው።
ከክላውድ ኮምፕዩቲንግ መምጣት በፊት፤ ሶፍትዌር የሚያመርቱ እና የሚጠቀሙ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ብዙ ዓይነት ሶፍትዌር እና ሃርድዌር ገዝተው ይጠቀሙ ነበር። ይህ ውድና ውስብስብ ከመሆኑም በላይ፤ ለአጭር ግዜ ብቻ መጠቀም የምንፈልገውን ሃርድዌር ከመግዛት ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረም። በዚህም ምክንያት ወደ ገበያ ለመግባት የሚፈልጉ ድርጅቶች ከጅምሩ ብዙ ወጪ ማውጣት ግድ ይላቸው ነበር። ድርጅቶች ከጅምሩ ምን ያክል የውሂብ ማጠራቀምያ (storage)፣ የማስያ ጉልበት (processing power) ወዘተ…. እንደሚያስፈልጋቸው በቀላሉ መገመት አይችሉም። ድርጅታቸው ከሚፈልገው በላይ ጉልበት ያላቸው ሃርድዌር ከገዙ ለአላስፈላጊ ወጪ ይጋለጣሉ፤ ካሳነሱት ደግሞ ሲስተማቸው ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ይቸገራል። ይህንን ዓይነት ችግር ለመፍታት ክላውድ ኮምፒዩቲንግ እጅግ ወሳኝ ቴክኖሎጂ ነው።
እንደ አማዞን፤ ማይክሮሶፍት እና ጉግል የመሳሰሉ ድርጅቶች ብዙ ክፍተኛ አቅም ያላቸውን ኮምፒውተሮችን አዘጋጅተው ለድርጅቶች እና ግለሰቦች ያከራያሉ። ለምሳሌ አንድ ሰው 100 ኮምፒተሮችን ተጠቅሞ ውስብስብ የሆነ የኮምፒውተር ሲሙሌሽን መስራት ቢፈልግ፤ 100 ኮምፒተሮችን መግዛት አይጠበቅበትም ማለት ነው። ከ አማዞን እነዛን ኮምፒተሮች ተከራይቶ ተገቢውን ሶፍትዌር ኮምፒተሮቹ ላይ በርቀት (ኢንተርኔት ተጠቅሞ) ይጭናል። የፈለገውን ስራ አከናውኖ የተገኘውን ውጤት ወደ ራሱ ኮምፒተር መውስድ ይችላል። ይህ ሰውዬ እንደዚህ በማድረጉ ብዙ ነገር አትርፏል። አንደኛ ስራው መጀመርያ እንዳሰበው በ 100 ኮምፒተሮች ብቻ የማይከናወን ከሆነ በቀላሉ ተጨማሪ ኮምፒተሮችን ማሰማራት ይችላል። ሁለተኛ ደግሞ ሰውዬው ክላውድ ኮምፕዩቲንግ ሲጠቀም የሚከፍለው ብር ልክ እንደ ውሃና ኤሌክትሪክ በተጠቀመበት መጠን በመሆኑ እነዛን 100 ኮምፒተሮች ለ አንድ ሰዓት ብቻ ከተጠቀመ የሚከፍለው በዛ ልክ ብቻ ነው። ይህም ክላውድ ኮምፕዩቲንግን እጅግ አስፈላጊ ከማድረጉም በተጨማሪ ተለጣጭ ወይም (elastic) ባህሪ ያለው ቴክኖሎጂ ያደርገዋል።
የክላውድ ኮምፒዊቲንግ ቀላል ምሳሌ ከፈለግን በሞባይላችን ውሂብ መጠባበቅያ (backup) ስናስቀምጥ፤ ኢሜል ስንጠቀም እና ሌሎች ነገሮችን ስናደርግ መረጃችን ያለምንም መጨናነቅ መቀመጣቸው የክላውድ አስፈላጊነትን በሚገባ ያሳዩናል። ስልካችን ቢጠፋም አስፈላጊውን ቅጽ በመሙላት የጠፉብንን ውሂቦች የምናገኘው በክላውድ የተነሳ ነው። ለምሳሌ ፌስቡክን ካየነው ሙሉ በሙሉ ክላውድ መሰረት ያደረገ አፕሊኬሽን በመሆኑ ኢንተርኔት እስካለን ድረስ ማንኛውንም ፌስቡክ ላይ ያደረግነውን እንቅስቃሴ በየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነን ማየት እንችላለን።
ምንጭ፡AD. Information Technology እና tech scieence bufe
@esafeSoftwareSolution
@esafeSoftwareSolution
749 views15:20