🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

#ኢትዮጵ #የወረርሽኝ_ታሪክ_በኢትዮጵያ የገዳዩ ወረርሽኝ (ኮሌራ) በሰሜኑ ክፍል እየቀነሰ መ | ኢትዮጵ

#ኢትዮጵ
#የወረርሽኝ_ታሪክ_በኢትዮጵያ
የገዳዩ ወረርሽኝ (ኮሌራ)

በሰሜኑ ክፍል እየቀነሰ መሄድ
ከምስራቅ የተነሳው የኮሌራ ወረርሽኝ በጥቅምት ወር 1865ዓ.ም. የወደብ ከተማ ከሆነችው ምጽዋ ደረሰ። የብሪቲሹ የመንግስት መልዕክተኛ Henry Blanc እንደሚለው ወረርሽኙ በምጽዋ ብዙ ጉዳት አድርሷል። በተለይም በቂ የሆነ ምግብ መመገብ የማይችሉትን ምስኪን ደሀዎች ወረርሽኙ በአስከፊ ሁኔታ ነበር ያጠቃቸው። በምጽዋ በወረርሽኙ ከተጠቁት አገግመው በህይወት የመትረፍ እድል ያገኙት ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። የአከባቢው አስተዳዳሪ የነበረው ፓሻ ሳይቀር በወረርሽኙ ብዙ ግዜ የሞትን ደጃፍ ከረገጠ ተመልሷል። ፈረንሳዊው የታሪክ ጸሀፊ Donin እንደሚነግረን ከሆነ በወቅቱ የኮሌራ ወረርሽኝ በጥቂቱ 300 የሚሆኑ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።
የምጽዋ ሰዎች ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ ለመከላከል ከወሰዱት እርምጃ አንዱ የንግድ እንቅስቃሴን ማቋረጥ ነበር። በዚህም መሰረት ወደ አከባቢው ለንግድ የሚንቀሳቀሱትን ነጋዴዎች ወደ ከተማው እንዳይገቡ እገዳ ጣሉ። ይህን ያድርጉ እንጂ ጥንቃቄው የወረርሽኙን ስርጭት ሳይገታው ወደ ትግሬና ወደ ሌሎች አውራጃዎች ሊስፋፋ ችሏል። እንደ Blanc ማስታወሻ በተለይም በትግራይ የከፋ ጉዳት ነበር ያስከተለው። እንደ እንግሊዛዊው Shepherd ዘገባ ከሆነ ደግሞ በእንጣሎ እና አከባቢው ወረርሽኙ የፈጀውን ፈጅቶ የቀረውም ሰው ቀዬውን ጥሎ በመሰደዱ አከባቢው ወና ቀርቶ ነበር። በዚህ ያልቆመው የኮሌራ ወረርሽኝ ወደ ደናኪል በመውረድ ብዙ ጥፋት እንዳደረሰ ከስዊዙ ተጓዥ Muzinger ማስታወሻ መረዳት ይቻላል።
አጼ ቴዎድሮስ
በግንቦት 1886ዓ.ም. በደቡብ ምስራቅ ጣና ሀይቅ ዳርቻ በምትገኘው ቆራጣ የኮሌራ ወረርሽኝ መቀስቀሱ ተሰማ። Blank እንደሚለው አጼ ቴዎድሮስ ይህን ወሬ እንደሰማ ወደ በጌምድር ደጋማ ስፍራ ለመጓዝ ወሰነና ወደዛው ከመንቀሳቀሱ በፊት የወረርሽኙን መጠን ለመገምገም ቆራጣ ቢሄድ በቀናት ውስጥ ወረርሽኙ የንጉሱን ካምፕ አጥለቀለቀው። በቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መርገፍ ጀመሩ። ጉዳዩ ያሳሰበው ቴዎድሮስ ወደ አክባቢው ተራራማ ስፍራ ወታደሮቹን ቢያንቀሳቅስም ወረርሽኙ ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ ሰው መጣሉን ተያያዘው። አብያተ-ክርስቲያናት በሰው ሬሳ ተሞሉ፣ ወደ ቤተክርስቲያን የሚወስዱ ጎዳናዎች ተኝተው የመጨረሻ የሞት ጣር ባነቃቸው የመላዕከ ሞት እጩዎችና ሞተው በወደቁ አስክሬኖች ተዘጉ። ከዚህ መዓት ጥቂቶች ቢተርፉ ፈንጣጣና ታይፈስ እየተፈራረቁ ተቀራጯቸው።

በጌምድር - ጎንደር
ከዚህ ብኋላ አጼ ቴዎድሮስ ወደ በጌምድር የመጓዙን ጉዳይ ስለወሰኑ ወታደሩና የተቀረው ሰው ወደ በጌምድር ጉዞውን ጀመረ። የጉዞውን ሁኔታ ለታሪክ በማስታወሻው ከትቦ ለታሪክ ያቆየልን Waldmeir እንደሚለው ጉዞው እጅግ አድካሚ ነበር። ወደ 100,000 የሚጠጉ ወታደሮች፣ ሴቶችና ህጻናት ነበሩ አንድ ላይ ታጭቀው የሚሄዱት። አንዳንዱ ህመምተኛ ነው፣ በመንገድ ላይ የሚሞተውም መዓት ነበር። የሞተውን የሚያነሳው ስለሌለ ያሁሉ ህዝብ ተረማምዶበት ሲያልፍ የሚወጣውን ጠረን፣ ለሞተ ዘመዳቸው ሰዎች የሚያለቅሱትን ለቅሶ መቋቋም እጅግ ሲበዛ ፈታኝና አሰቃቂ ነበር።

የንጉሱ ምርመራ (Inquiry)

አጼ ቴዎድሮስ አብረዋቸው የነበሩትን የውጭ ሀገር እስረኞች መላ አምጡ ማለት ጀመሩ። እንዲህ ዓይነት ወረርሽኝ ሲያጋጥማቹ በሀገራችሁ ምን ታደርጋላችሁ? ሲሉ ጠየቋቸው። Henry Blanc ለዚህ ለንጉሱ ጥያቄ ወደ በጌምድር ተራራማ ቦታዎች መንቀሳቀስ እና በተቻለ መጠን ወታደሩን መበተን የተሻለ እንደሆነ ሀሳብ አቀረብን ይላል። አጼ ቴዎድሮስም የተባሉትን ምክር በመቀበል እንደታባሉት አደረጉ።
በግዜው በአጼ ቴዎድሮስ እስር ላይ የነበረው Henry Blanc ከእስር ተፈቶ ብዙዎችን ማከሙና ማዳኑ ይነገራል። ወታደሮቹን የመበተኑና ወደ ደጋማው ስፍራ የመሸሹ ምክርም ውጤታማ ሆኖ ወረርሽኙ መቀነስ አሳይቷል። በግዜው የነበረውን ሁኔታ Blanc ወረርሽኙ ሙሉ በሙሉ በመጥፋቱ ንጉሱ ደስተኛ ነበር ሲለን Waldmeir በበኩሉ ይህን የሚያጠናክር ሀሳብ በማስታወሻው አስፍሯል። እንደ ህክምና ታሪክ ጸሀፊው Hirsch ዘገባ ግን ወረርሽኙ የሰሜን ተልዕኮውን አጠናቆ ወደ ደቡባዊው የሀገሪቱ ክፍል ለማቅናት ያኮበኮበበት ግዜ ነበር።
ከዛስ ምን ተፈጠረ? በሚቀጥለው ክፍል ይጠብቁን።

ይቀጥላል.....