🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

ዋ!…ያቺ ዓድዋ ዋ!… ዓድዋ ሩቅዋ የዓለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ ዓድዋ… | ስለ መፅሀፍት በጥቂቱ

ዋ!…ያቺ ዓድዋ
ዋ!…
ዓድዋ ሩቅዋ
የዓለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ
ዓድዋ…
ባንቺ ብቻ ሕልውና
በመስዋዕት ክንድሽ ዜና
አበው ታደሙ እንደገና
ዋ!
ዓድዋ የዘር ዐፅመ ርስትዋ
የደም ትብያ መቀነትዋ
በሞት ከባርነት ሥርየት
በደም ለነፃነት ስለት
አበው የተሰውብሽ ለት
ዓድዋ
የኩሩ ትውልድቅርስዋ
የኢትዮጵያነት ምስክርዋ
ዓድዋ
የኩሩ ደም ባንቺ ፅዋ
ታድማ በመዘንበልዋ
አፅምሽ በትንሣኤ ነፋስ
ደምሽ በነፃነት ሕዋስ
ሲቀሰቀስ ትንሣኤዋ
ተግ ሲልሲንር ትቢያዋ
ብር ትር ሲል ጥሪዋ
ድው እልም ሲል ጋሻዋ
ሲያስተጋባ ከበሮዋ
ሲያስገመግም ዳኝው መድፍዋ
ያባ መቻል ያባ ዳኝው
ያባ ነፍሶ ያባ ቃኝው
ያባበለው በለው ሲለው
በለው- በለው-በለው-በለው!
ዋ!…ዓድዋ…
ያንቺን ፅዋ ያንቺን አይጣል
ማስቻል ያለው አባ መቻል
በዳኘው ልብ በአባ መላው
በገበየሁ በአባ ጎራው
በአባ ነፍሶ በአባ ቃኝው
በለው ብሎ፥በለው-በለው!
ዋ!…ዓድዋ…
ዓድዋ የትላንትናዋ
ይኸው ባንቺ ሕልውና
በትዝታሽ ብፅዕና
በመስዋት ክንድሽ ዝና
በነፃነት ክንድሽ ዝና
በነፃነት ቅርስሽ ዜና
አበው ተነሱ እንደገና
…ዋ!…ያቺ ዓድዋ
ዓድዋ ሩቅዋ
የአለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ
ዓድዋ…
የካቲት(፲፱፻፷፬-ዓድዋ)
ከ ፀጋዬ ገብረ መድህን