🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

#የጥቁር_ህዝብ_ኩራት #ዓድዋ_125 #ዝክረ_ዓድዋ እቴጌ ጣይቱ | ስለ መፅሀፍት በጥቂቱ

#የጥቁር_ህዝብ_ኩራት
#ዓድዋ_125
#ዝክረ_ዓድዋ

እቴጌ ጣይቱ ብጡል «እኔ ሴት ነኝ፣ጦርነት አልወድም፣ሆኖም ግን ኢትዮጵያን የጣሊያን ጥገኛ የሚያደርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ ፡፡ »

የጦርነቱ መነሻ ምክንያት

የዓድዋ ጦርነት መነሻ ምክንያት የሆነው የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ሲሆን ይህ አንቀጽ የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተን ሆኖ በመገኘቱ እንዲሰረዝ የተደረገው ሙከራም በጣሊያን እምቢተኝነት በመክሸፉ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።

የጣሊያን ወረራ መሰማትና እቴጌ ጣይቱ

የጣልያንን እምቢተኝነት ተከትሎ ሚኒስትሮች፣ የጦር አለቆችና መኳንንቱ ባካሄዱት የምክክር ጉባኤ ላይ እቴጌ ጣይቱ ብጡል «እኔ ሴት ነኝ፣ጦርነት አልወድም፣ሆኖም ግን ኢትዮጵያን
የጣሊያን ጥገኛ የሚያደርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ ፡፡ » ሲሉ የሰጡት አስተያየት ነበር፡፡

የኢትዮጵያው ንጉሰ ነገስት የዳግማዊ አጤ ምኒሊክ የክተት አዋጅ

ጣሊያን ውል አፍርሶ ኢትዮጵያን ሲወርር በጉልበቱ የጀግኖችን ሃገር ሊፈታው እንደማይችል ያውቅ ነበር። ጣልያን በልዩነታችን ገብቶ ሊለያየን እቅድ አቅዶም ነበር ። ይህንንም
ለማሳካት በተለያየ አስተዳደር ግዛት ለይተው በሚቆራቆሱ የጦር አበጋዞችና በንጉሱ መካከል የነበረውን የከፋ ልዩነት መጠቀም ለድል እንደሚያበቃው አልሞ መነሳቱ እውነት ነበር ።

ያም ሆኖ የንጉሰ ነገስቱ መኳንንቱን ፣ ሹመኞችን እና የጦር አለቆችን ሰብስበው በመምከር ብሔራዊ ክብርን ማስጠበቁ ይቅደም አንድምታ ያለው ሃሳባቸው ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ በሰለጠነ መንገድ ከመግባባት ላይ ደረሱ። ይህም ምክክርና ስምምነት
ሁሉም በአንድነት ለነጻነትና ክብሩ ይተጋ ዘንድ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደርግ ዘንድ ሁሉም በየስራ ድርሻው ተመድበው መስራት ጀመሩ።

መስከረም 1888 ዓ.ም ወር ላይ ንጉስ ምኒሊክ ጣሊያንን ለወረራ መዘጋጀቱን በስለላ ባለሟሎቻቸው በቅርብ አረጋገጡ።

በወረራ ዝግጅቱ የተቆጡት ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ የክተት አዋጅ
እንዲህ በማለት አስነገሩ …

‹‹እግዚአብሄር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአ ብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት
ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ
ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን
አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት
የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም…››

ዓድዋና የጦሩ ዝግጅት

የዓድዋው ጦርነት በጣልያኖች በኩል የቆየ የቀኝ ግዛት ጥማቸውን ለማሳካት ቀድሞ የተጠነሰሰ ነበር። በኢትዮጵያውያን ዘንድ ግን የጦርነት ዝግጅቱ እስከ ሰባት ወር የፈጀ እንደነበር ይነገራል። ዝግጅቱ ተጠናቆ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ጎህ
ቀዶ እስኪጠልቅ በቀድሞዋ ትግራይ ጠቅላይ ግዛት በዛሬዋ ክልል አንድ ትግራይ ውስጥ በምትገኘው በዓድዋ ከተማ ይገጥም ዘንድ ቀኑ ደረሰ ! በዓድዋው ዘመቻ በመቶ ሺሕዎች
ሆኖ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ከጥቂቱ በስተቀር አብዛኛው ጦር፣ ሰይፍ፣ ጋሻና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ይዞ እንደ ነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

ጣሊያን በአስር ሽዎች የሰው ሃይል ፣
በዘመናዊ የጦር መሳሪያና በወታደራዊ ሳይንስ የሰለጠነ አውሮፓዊ ጦር ነበርና ከፍ ባለ ስንቅና ትጥቅ ተደግፎ ወረራ
መጀመሩ ይጠቀሳል።

አንጸባራቂው የዓድዋ ድል !
የጥቁሮች ድል !

የጣሊያን ጦር በጄኔራል ባራቴሪ እየተመራ ባህር ተሻግረሮ ሲመጣ የተወረረችው የኢትዮጵያውያን ጦር
የሚመራው በንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ ነበር። ጀግና ብልህና አርቆ አስተዋይዋ ባለቤታቸው እትየ ጣይቱ ብጡል በዚያ ባልሰለጠነ ዘመን ስልጡን ነበሩና በባለቤታች ከሚመራው የአርበኞች ግንባር እኩል ተሰልፈው ሃገሬውን ስንቅ ትጥቅ
በማስታጠቅና በማበረታታት የከፈሉት መስዋዕትነት ቀላል አልነበረም።

ኢትዮጵያውያን በንጉሱ ብልህ አመራርና ክተት ብለው በህብረት ተነሱ ። ከሽኩቻና ዝብሪት ተዘፍቀው የባጁት
የየግዛቱ ሹሞች እና የጦር አበጋዞችም በንጉሰ ነገስት አጤ ምኒሊክ የክተት አዋጅ ልዩነታቸውን አስወግደው በህብረት ተመሙ !

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ከ124 ዓመታት በፊት በዕለተ ሰንበት ክብሩ የተነካው አርበኛ ህዝብ ዓድዋ ላይ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ተንቀሳቅሶ ባካሔደው ውጊያ እብሪተኛውን
ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ የጣሊያን ጦር ጋር ገጠመ !

ከማለዳ አንስቶ ጀንበር እስክታዘቀዝቅ ባለው ጊዜ የተካሄደው ጦርነት እልፍ አእላፍ መስዋዕት ሆነው በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት በዓድዋ ተደመደመ !
ጣሊያን ከአንባላጌ እስከ አድዋ ተጠራርጎ እንዲወጣ ያደረገው
” የጥቁሮች ድል!” በሚል አለም ባወደሰው የዓድዋ ድል የጣሊያን መንግስት የሃፍረት ማቅን በግዱ ተከናነበ።

የዓድዋ ድል በመላ በአለም ከተበሰረ በኋላ የወረራው መነሻ የሆነውን የውጫሌ ውል ፈርሶ የጣልያን መንግስት በውጫሌ ውል
የነበረውን አጉል ምኞቱን ይሰርዝ ዘንድ ግድ ሆነበት ።

ወራሪው በሽንፈቱ አፍሮ የኢትዮጵያን ሙሉ ነፃነት አውቆ እና ተቀብሎ
የሰላም ስምምነት ያደርግ ዘንድ ተገደደ ! የስምምነት ውሉም ለአለም መንግስታት ተሰራጨ። ውሉ የደረሳቸው መንግስታት እና ሃገራት የኢትዮጵያን የተረጋገጠ ሉአላዊ መንግስትነት በውድም ሆነ በግድ ተቀብለው አረጋገጡት !

ይቀጥላል………