Get Mystery Box with random crypto!

የህይወታችንን ትርጉም የምንፈጥረው እኛው ነን፤ ህላዌነት(existentialism) ሰው ሆኖ የመኖ | ስለ መፅሀፍት በጥቂቱ

የህይወታችንን ትርጉም የምንፈጥረው እኛው ነን፤

ህላዌነት(existentialism) ሰው ሆኖ የመኖርን ጉዳይ ይፈትሻል፡፡ የህላዌነት እሳቤ ተከታዮች እንዲህ ይሉናል፡፡ ሰው ወደዚህ አፅናፈ-ዓለማት (ዩኒቨርስ) ተጣለ፡፡ እውነታውም በዚህ ምድር ላይ እንደ አጋጣሚ መጣን እንጂ ታስቦበትና ለአንድ አላማ ብቻ አልተፈጠርንም ይላሉ፡፡ ሰው ማሰብ የሚችል ግለሰባዊ ፍጡር እንደሆነ፣ በነፃነት ማናቸውንም ነገር ማድረግ እንደሚችልና ሕይወቱም የሚገለፀው እራሱ በመረጠው መንገድ እንደሆነም ያምናሉ፡፡ በዚህም መሰረት፣ የሕይወቱ እሴቶችና አላማው የሚወሰኑት በግለሰቡ ሀሳብ እና ምርጫዎቹ ላይ ነው።

ህላዌያዊያን ሁሉም የሰው ልጆች የማይናወጥ ነፃ ፈቃድ እንዳላቸው ያስረግጣሉ፡፡ ነፃ ፈቃድ የመኖር እውነታ ደግሞ ወደ ሕይወት ምርጫ ይመራናል፡፡ ግላዊ ምርጫዎች እንደ ግለሰቡ ፈቃድ የተለያዩ ሲሆኑ፣ መነሻቸውም በግለሰቡ እይታና ተሞክሮ ላይ የሚመሰረቱ እንጂ፣ በውጫዊ ኃይል ወይም በማህበረሰቡ ላይ የሚደገፉ መሆን የለባቸውም፡፡ ሰዎች በእነዚህ ምርጫዎች ላይ ተመርኩዘው ማን እንደሆኑና ምን እንደሆኑ መረዳት ይጀምራሉ፡፡

ህላዌነትን የተቀበሉ ሰዎች፣ እግዚአብሔር (ፈጣሪ) ስለመኖሩ ወይም
ስላለመኖሩ ለማረጋገጥ ጥረት አያደርጉም፡፡ ይልቁንም የህላዌነት አቢይ ሀሣቦች (እንደ ሙሉ ነፃነት) በኃይማኖተኞች ዘንድ ፈጣሪ የሚባለው ሙሉ በኩልሄ የሆነ፣ ሁሉን አዋቂ፣ ሁሉን ቻይ፣ ሁሉ ቦታ የሚገኝ፣ ሁሉ በሁሉ መልካም የሆነ አካል አለ ከሚለው ሀሣብ ጋር ስለማይጣጣም ነው፡፡ ህላዌነት ሰዎች በራሳቸው ጥረት የራሣቸውን የሕይወት ትርጉም እና አላማ ፈልገው እንዲያገኙ የሚገፋፋ እንደመሆኑ፣ በሕይወታችን ላይ ተፅዕኖ ማሣረፍ የሚችል አንዳችም ውጫዊ ሃይል አለ ብሎ ማመን በራሱ ለዚሁ የህይወትን ትርጓሜ ፍለጋ እንቅፋት መሆኑ ግልፅ ነው።