🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

..................... ፪ ............... የቀጠለ .... ... ሌላው የደራሲ | ስለ መፅሀፍት በጥቂቱ

..................... ፪ ...............
የቀጠለ ....
...
ሌላው የደራሲ ሀብታሙ አለባቸው ጥልቅ የፖለቲካ አረዳድ ችሎታ ሶቬት ህብረቱን ሊቀመንበር ሚካኤል ጎርቫቾቭ የሶሻሊስት ርዕዮተ አለም ትንታኔ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አዛምዶ የሚያቀርብበት ስነዳ የደራሲው እምቅ የአረዳድ ችሎታ ሀሳቡን የሚሰማ ትውልድ ካለ ጠቃሚ ነጥቦችን በማሳረፍ ለውጥ ውሃ እንደጠማው የበረሃ ተጓዥ መንገደኛ ጥሟን የሚከላ ነው ብዬ አስባለሁ።
ደራሲው ሀብታሙ አለባቸው ስነፅሁፍንና አብዮት ነክ የታሪክ አተራረክ ፍሰትን የራሱ በሆነ ቀለም ለዘመናችን በሚመጥን ዘውግ አዲስ ነገር ፈጥሯል ብሎ ለማለት ቀደምት ስራውን የሱፍ አበባን እና የቄሳር እምባን ሁለት ድንቅ ልቦለዶች ማንበብ በቂ ሲሆን ረቂቁን አይቶ ጀርባው ላይ አስታየቱን ያሰፈረለት የአዲስ አድማሱ አምደኛ አቶ ደረጀ ይመር " ከአወዛጋቢው ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ በኃላ ስነ ፅሁፍንና ፖለቲካን " ድል ባለ ሰርግ" ያጋባ ደራሲ አቶ ሀብታሙ አለባቸው ይመስለኛል' እንዳለው እኔም በሀሳባቸው እስማማለሁ።
አብዮቱ ኢትዮጵያ ላይ ያሳረፈውን ጥቁር ጠባሳን በማሳየትም የልጅን አስክሬን ለመቅበር የጥይት ፍሬ ገንዘብ ከፍሎ ከማንሳት ወላጅን አለ ጧሪ ቀባሪ የማሳጣት እንዲሁም ሁለት ወንድማማች ሀገሮችን ለስልጣን ጥም ሲባል በፖለቲካ ደባ ህዝብ ማለያየት ፣ ንፁሃንን አለርህራሄ መግደል፣ ሀብት መዝረፍ፣ቤተሰብ ውበቷ ያማረ ልጅ ካለውም በሞት አስፈራርቶ መንጠቅና መድፈር ያሉትን የአብዮቱ ዘመን መገለጫ የነበሩ ትዕንቶች በአይነ ህሊናችን እንዲቀረፅ በብርቱ የተጋበት ፈርጅ ደራሲው የተዋጣለት የአተራረክ ዘውግን በመከተሉ ቆመን የምናጨበጭብለት ነው።
እንደመዝጊያ ይህን መሰል የአንድ ዘመንን አኗኗር ፣ የአስተሳሰብ ብስለት፣ የኑሮ ውጣ ውረድ፣ የመሪና የህዝብ ግንኙነት ስራን አበክሮ ለታሪክ ማቆየቱ አንባቢ ፊደላቱን መቁጠሩና መደርደሪያው ላይ ከመሰብሰቡ ባለፈ ከዘመን ተምረን የተሻልን እንድንሆን የሚያነቃ ትልቅ ማስተማሪያ ነው ብዬ አምናለሁ።
ባለንበት እየረገጥን ዘላለም በህዝብ እና በሀገር እየተማረርን ኑሯችን ከእጅ አይሻል ዶማ እንዳይሆን እነዚህን መሰል መፅሀፎች እንደትልቅ መስታወት ራስን መመልከቻ መንገዶች ናቸው ብዬ አምናለሁ።
የቱ ጋ ነኝ? ወደ የት ነው ጉዞዬ? መጨረሻዬስ? የሚሉ ብርቱ ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎችን በመፍታት በማህበረሰብ ንቃተ ህሊና አልያ በሀገር ላይ የሚነሳን ህዝባዊ አመፅ ለመግታት እንደ ሀብትሽ ያሉ ጀግና ደራሲያን ያስፈልጉናል ባይ ነኝ።
አሁንም አበክሬ የምናገረው የቄሳር እምባን የመሳሰሉ በብስለት የተፃፉ መፅሀፍት ለሀገር እድገት ከፍታ የሚውሉት ውለታ ይህ ነው የሚባል አይደለም።
አንባቢው ከመቶ አለቃ በላይ እና ሀምራዊት የከንፈር መሳሳምና የአልጋ ትይንት ባለፈ ወይም በኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም አስቂኝ ና አይረሴ ስድቦች ባሻገር እንደሀገር የሚለውጡን በርካታ ሀሳቦች ላይ ማተኮር ቢቻል ብዬ እያሳሰብኩ እንደመዝጊያ ከመቶ አለቃ በላይነህ " የልግመት ኢትዮጵያ " ጥናት ውስጥ የሚካኤል ጎርባቼቭን በዘመን መካከል ፀንታ የምትቆይ አባባል ላንሳና እንሰነባበት እነሆ፦
..... " የልግመት ሶሻሊዝም ምልክቶች አንዱ የህዝብ ተስፋ መቁረጥ ነው። ያኔ ለመንግሥት ተቋማት አክብሮት አይኖረውም። ህግን የሚጋፋና ረብሻ ወዳድ ትውልድ ይፈጠራል።
ሱቅ ይገባል። ገንዘብ አይከፍልም። ያገኘውን ይዞ ይሮጣል።
በትንሽ አለመግባባት ግጭት ይቀሰቀሳል፣ ይደባደባል ፣ ይገዳደላል...። የትም ሶሻሊዝም ሀገር ሂዱ። ይህ ቀውስ መዋቅራዊ መልክ ይዞ ታገኙታላችሁ።"....
................. ገፅ 162 ..........
አንድ ያጣላልና አለፍ ብለን አንድ እንድገም ፦
...... " ሕዝብ አዲስ ነገር መፍጠር እንዳይችል እጁ ተጠፍሮ ሲያዝ መልሱ እምቢ ነው።
በዚህ ጊዜ በሶሻሊዝም ካባ የተጀቦነው መንግስት የግዳጅ መዶሻውን ያገሳል።..."
....................ገፅ 225 .........
የቄሳር እምባ ምንድነው?....ማነውስ ቄሳር?..... የጅማው አስተዳዳሪ የይማም ሚስት ሀምራዊትና የመንግስቱ አማችና አማካሪ የሆነው የሊቁ መቶ አለቃ በላይነህ የስውር የፍቅር ግንኙነትስ የት ድረስ ይዘልቃል?.... ይማም ለአመታት ከከረመበት ግዳጅ ሲመለስስ በሚስቱ በባላንጣውና በእሱ በኩል ምን ይፈጠራል?....መቶ አለቃ በላይነህን ትንፋሹ እስኪቆም ያስደነገጠው የጠፋው የግል ሚስጥራዊ ማስታወሻ ደብተሩስ ይገኝስ ይሆን..?...ማስታወሻው ላይ የተፃፉ አደገኛ ፅሁፎችንስ መንግስቱ ሀይለማሪያም ያነቡት ይሆን? ...የመንግስቱን የግል ጠባቂ መቶ አለቃ ምስጋናውንስ ማን ገደለው?......ይህንና መሰል ምስጢሮችን ለመፍታት የቄሳር እምባን ያንብቡ.... ደራሲውን በጥልቀት ለመተዋወቅም የሱፍ አበባን እና በቅርቡ ለህትመት የበቃውን ሕንፍሽፍሽ የተሰኘ መፅሀፉን ያንብቡ
አበቃሁ!