🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

የፕ/ት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመቐለ ጉብኝት... ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በትግራይ ክልል መቐለ | ገራዶ ሚዲያ

የፕ/ት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመቐለ ጉብኝት...

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎችን ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸውም በመቐለ ከተማ የሚገኙትን የዓይደር ስፔሻላይዥድ ሆስፒታል፣ የፌደራል መንግስት እህል ማከማቻ ማዕከላዊ መጋዘን እና በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በከተማዋ የሚገኙ ተፈናቃዮችን አይተዋል፡፡

ፕሬዘዳንቷ ከመቐለ የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ጋርም ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱም የአገር ሽማግሌዎች በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል የተንሰራፋው የሥራ አጥነት ችግር እንዲፈታ፣ ከመንግስት ቢሮዎች የተዘረፉ ቁሳቁሶች ተሟልተው በተጠናከረ መልኩ ስራ እንዲጀምሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በትግራይ በአሁኑ ወቅት በዋናነት ለሰላም እና ለጤና ቅድሚያ ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡ በተጨማሪም መንግስት እያቀረበ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት አጠናክሮ እንዲቀጥል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሰጡት ምላሽም ትግራይን ወደቀደመው ሰላም ለመመለስ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡ በትግራይ ክልል መንግስት ህዝብ አብሮ የሚኖርበትንና የሚደጋገፍበትን ስርዓት በመገንባት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል ያሉ የሕዝብ ጥቄዎች በአፋጣኝ እንዲፈቱ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ክልሉን መልሶ በማደራጀት ሂደት ውስጥ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ትብብር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ፕሬዚዳንቷ በመቐለ ያደረጉትን ጉብኝት በማጠናቀቅ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

t.me/geradomedia