🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

የአፋር ክልል በትግራይ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አደረገ! የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳ | ገራዶ ሚዲያ

የአፋር ክልል በትግራይ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አደረገ!

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ የአፋር ክልል ሕዝቦች በትግራይ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ያበረከቱትን ድጋፍ ተቀብለዋል። የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ሕዝብ ከዘጠኝ ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ድጋፉን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኤለማ አቡበከርና የአፋርን ሕዝብ የወከሉ የሃገር ሽማግሌዎች መቐለ ተገኝተው አስረክበዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ የአፋርና የትግራይ ሕዝቦች በደምና በታሪክም የተሳሰሩ፣ መቼም መለያየት የማይችሉ ናቸው ብለዋል፡፡

የትግራይ ሕዝብ ከገጠመው ችግር እንዲወጣ ሁልጊዜም ከጎናቸው ያልተለዩ መሆናቸውንም ገልፀዋል። የዛሬው ድጋፍም የአፋር ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብ ያለውን አለኝታነት የገለጸበት መሆኑን ነው የተናገሩት።

የሁለቱ ሕዝቦች ወንድማማችነትና ትስስር ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚጎለብት መሆኑንም ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡ ድጋፉ የመልካም ጉርብትና መገለጫ መሆኑን በመጥቀስ የአፋርን ሕዝብና መንግስትንም አመስግነዋል፡፡

የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኤለማ አቡበከር ሁለቱ ሕዝቦች ችግሮችና መልካም አጋጣሚዎችን በጋራ ያሳለፉ መሆናቸውን በማውሳት የትግራይ ሕዝብ ለደረሰበት ጉዳት ከ2 ሺህ 700 ኩንታል በላይ የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባ አስተዳደር በትግራይ ለተጎዱ ወገኞች ድጋፍ አድርገዋል። #ENA

t.me/geradomedia