Get Mystery Box with random crypto!

አንድ መንፈሳዊ ሚስጥር ላካፍላችሁ! ሰዎች በተለይም ክርስቲያኖች አብዛኛውን ጊዜ የሚሰሩት ስህተት | GOD'S GOSPEL

አንድ መንፈሳዊ ሚስጥር ላካፍላችሁ!

ሰዎች በተለይም ክርስቲያኖች አብዛኛውን ጊዜ የሚሰሩት ስህተት ሰይጣንን ተጠያቂ ማድረግ ነው። በአገልግሎት፣ በትምህርት፣ በቢዝነስ፣ ከሰዎች ጋር በለ ግንኙነት እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ለሚደርስብን እክል ወይም በሕይወታችን ወደፊት ለመሄድ ስንቸገር፣ ለውጦች እየፈለግን የምንፈልጋቸውን ለውጦች ግን ማየት ስያቅተን ሰይጣንን ተጠያቂ ማድረግ የተለመደ ነው፣ የሆነ ቦታ ለመድረስ እየፈለግን ነገር ግን ካለንበት ወደፊት ጠጋ ማለት ሲሳነን ሰይጣን ነው የከለከለኝ ስንል ብዙ ጊዜ እንደመጣለን። ይሄ ፈጽሞ ስህተት ነው፣ ወዳጆች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ በእኛም ምትክ በሰይጣን ለይ ፍጹም ፣ ዘላቂ ፣ የመጨረሻ እና የማይቀለበስ ድል ተቀዳጅቷል! ይህ ድል የክርስቲያኖችም ነው። ይሄ ማለት ሰይጣን እጁን አጣምሮ ይቀመጣል ማለት አይደለም፣ ነገር ግን የቱንም ያህል ቢዋጋ የተሸነፈ ነው። ስለዚህ ክርስቲያን በሕይወቱ ለሚከሰቱ መጥፎ ነገሮች ሁሉ ሰይጣንን ተጠያቂ ማድረጉ ለተሸነፈ ጠላት እውቅና (Credit) እንደመስጠት ያለ ሞኝነት ነው፤ እንደዚህ ያለው አስተሳሰብ ሰይጣንን የሚያከብር እና ኢየሱስ ክርስቶስ በሰይጣንና በጨለማ ሃይላት ሁሉ ላይ የተቀዳጀውን ድል የሚያኮስስ ነው።

ታዲያ ማነው ተጠያቂ? ወደፊት ላለመሄዴ፣ አንድ ቦታ ለመቆሜ ወይም ለመጥፎ ነገሮች ማነው ተጠያቂ? እራሴው ነኝ! በውስጤ ያለው አሮጌው ሰው ነው። ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ በኤፌሶን 4፥22 ላይ -“አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥” የሚለን። አሮጌው ሰው የሰይጣን አቻ ነው፣ ምንአልባትም የከፋ ይሆናል፣ ሰው ለሰይጣን ጥቃት እንኳ የሚጋለጠው በአሮጌው ሰው ምክንያት ነውና።

የዕብራውያን መልእክት ጸሓፊ ክርስቲያኖችን እንደዚህ በማለት የተናገረውም በዚሁ ምክንያት ነው---“እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” — ዕብራውያን 12፥1-2--- በዚህ ጥቅስ ውስጥ የተሰመራውን ተመልከቱ፣ ኃጢአት የሚለው ቃል የሚገልጸው የግብር ኃጢአትን ብቻ አይደለም ነገር ግን በውስጣችን ያለውን አሮጌውን ሰው ነው፣ ይህ ሰው ኃጢአተኛ ተፈጥሮ ያለው ሰው ነው። በግልጽ እንደምናነበው ይህንን አሮጌ ሰው ይህ ክፍል "ሸክም" እና "ቶሎ የሚከብ ወይም በቀላሉ ተብትቦ የሚይዝ" ይለዋል። ወዳጆቼ ክርስቲያኖች ወደፊት እንዳንሮጥ ሸክም እና በቀላሉ ተብትቦ የሚይዝ እና ያለንበት የሚያስቆም ጠላት የሆነብን ሰይጣን ሰይሆን በእኛ ያለው አሮጌ ሰው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ "አስወግዱት" ነው የሚለን። ይህንን አሮጌ ሰው ከስወገዳችሁ ሰይጣን በእናንተ አንዳች የለውም!

ወደ ግባችሁ ለመድረስ ሸክም የሚሆንባችሁን እና በቀላሉ ተብትቦ በፊታችሁ ከተዘጋጀው የከበረ ሩጫ የሚያስቆማችሁን አሮጌውን ሰው አስወግዱት! ፀጋ ይብዛላችሁ!

ተወዳጆች ሌሎችም መንፈሳዊ መልእክቶች ለማግኘት ቻናሌን ተቀላቀሉ

@TheDeepThingsOfGod
@TheDeepThingsOfGod