🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

ቸኮልሽ ለትዝታ ሁሉንም አጠናሁ :ሀሳብሽን አየሁት ያልሽውን ነገሩኝ : ቃልሽን ሰማሁት ከአሁን | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ቸኮልሽ ለትዝታ


ሁሉንም አጠናሁ :ሀሳብሽን አየሁት
ያልሽውን ነገሩኝ : ቃልሽን ሰማሁት
ከአሁን ታሪክሽ : የኔን ስም አጣሁት

በምኔው ተጣደፍሽ : እንዴት ረሳሽኝ?
በየት በየት አርገሽ : ከዛሬሽ ላይ ፋቅሽኝ?

የት ሄዶ ነው ሲሉሽ
ማነው ደሞ እሱ? ብሏል አንደበትሽ
እንደምን ነው ሲሉሽ
አላውቀውም ኧረ - ሲለኝ ሰምቻለሁ -
ኮልታፋው ምላስሽ
እውን ረሳሽኝ : ስሜን አጠፋሽው?
ከሙሉ ህዋስሽ : ጨክነሽ ሰረዝሽው?

አወ በፊት ያኔ : ወዳጄ ነበረ
በቃ በቃ በቃ : በቃ ድሮ ቀረ....

ያገኘሁሽ አምና ፡ የሄድኩ ትናንት ማታ
ምነው ወዳጄ ሆይ ፡ ቸኮልሽ ለትዝታ

የምር አትረሽኝም : አትበይ አላውቀውም
እንዳልጨከንኩ ያውቃል...
እኔን ሚረሳበት : ልብሽ ልብ የለውም
አትወጂኝ ይሆናል : ግን አትዘነጊኝም
ልብሽን ጠይቂው : ማነህ አትይኝም

ረሳሽው እንዴ???

ልክ ስትደነግጪ
የኔን ስም ነበረ : አፍሽ የሚጠራው
እንዲያምኑሽ ስትሺ
በኔ ስም ነበረ : ምህላሽ ሚሰራው
እሱን ይንሳኝ - እሱ ይሙት - ከእሱ ልጥፋ
ከቃሌ ጋር - አንዳች ሀሰት - ከተተፋ
ብለሽ ነበር
ረሳሽው
ድሮ ቀረ
ብለሽ አልሽው

ያገኘሁሽ አምና ፡ የሄድኩ ትናንት ማታ
ምነው ወዳጄ ሆይ ፡ ቸኮልሽ ለትዝታ
ምንን እንዲያውቁልሽ : ምንን ለመናገር
የትናንቱን ንጉስ - (አላውቀውም ብሎ) -
እንደሎሌ መቁጠር

...ደሞኮ ያውቁብሻል
አላውቀውም ስትይ : ስስት ያዩብሻል
እንባ ያነቡብሻል
ህመም ይሰሙሻል
(ናፈቀች ይሉሻል)

እኔም አውቅሻለሁ
ማነው እሱ? ስትይ አካልሽ አሞታል
ልብሽ ተሰምቶታል
ህሊናሽ ገርሞታል
አይንሽ ለብልቦታል
ውስጥሽን በርዶታል...

ከልብሽ አደለም : ዘግተሽ ያባረርሽኝ
ላንደበትሽ ነበር...
ከዛሬሽ የተፋኩ : ትዝታሽ ያረግሽኝ
ላትችይው ነገር : ችለሽ ላትገፊበት
ረሳሁት እያልሽ : ስሜን አፌዝሽበት
ሰማሁና አዘንኩኝ : አነባሁኝ ላንቺ
ረሳሁት ስላልሽ - የረሳሽኝ መስሎሽ -
ስላየሁ ስትስቺ

ልብሽ ያዘዘበት : ይሄ ያልታደለው
ጨካኝ አንደበትሽ...
'እንጃ' እያለ ሲጮህ : መርሳትን ያልቻለው
...ይሄን ብሎ እኮ ነው
ከገቡ በኋላ : ማንኳኳት ምንድን ነው??

አንቺም ከፋሽበት...
ልብሽ ልቡን ነሳው : ልቤም አዘነለት
አሁን ምን ይባላል : ተኩሶ ቁም ማለት?
...ወደህ እርሳ ማለት?

ያገኘሁሽ አምና ፡ የሄድኩ ትናንት ማታ
ምነው ወዳጄ ሆይ ፡ ቸኮልሽ ለትዝታ?


በአቤኒ የተፃፈ

ከወደዱት ለወዳጆ ያጋሩ
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19