. በሁሉ የደመቀው : ደብዝዟል ያ መልኳ ቀሚሷ ይመስክር : ነውር ሆኗል ልኳ ማንም የሚስመው : ቀልቷል አብጧል ፊቷ የተመካችበት : ፈርሳለች ጣኦቷ ኪዳን የማታውቀው : ጣቷ ኮስምናለች ቀድማ የወጣችላት : ፀሀዩኣ ጠልቃለች ሲነኳት ተሰብራ : ሲገፏት ወድቃለች ሳታቃስት ሙታ : በቁም ተቀብራለች . . . አልቃሽ አጣችና ሙሾ አውራጅ ጠፋና በራሷ ቀብር ላይ : ራሷ አለቀሰች ራሷ ለስሟ : ሙሾን አወረደች (ለኔ ያርግ እያለች) ገላዋን ጨክና : አፈር አለበሰች ....ሩጫ ጨረሰች? ከዛ ቀን በኋላ ያማት አልተገኘም : የሚያነሳ ስሟን ነውሯን የሚያነውር : የሚሰብር ቅስሟን የት ጠፍታ ነው? የሚል : አስታዋሽ አልመጣም ደበዘዘች የሚል : ከአፍ ውስጥ ቃል አልወጣም በአንድ እብድ ገመድ ያላበደ ንፋስ : የሚወዘውዘው ቀሚስ ይዘምራል መዝሙሩን ሲሰማ ከደመና በላይ የመነነ ውብ ጥርስ : ደርሶ ፈገግ ይላል ቀሚሱ ሲዘምር..... ጨዋ እንደነበረች : ጨዋነት ነፈጓት ቆንጅየ ነበረች : ውብ መልኳን ገፈፏት ለባሽ አድማቂየን : እንቡጤን ቀጠፏት (ቀጥፈውስ መች ተዋት) ለእድፍ ለነውራቸው : አረጓት ተከሳሽ ለመርገፋቸው ልክ : አረጓት ስም ወራሽ በስንት ልመና በፀበል በፀሎት : ብታገኝ እብደቷን ይተራመሳሉ ሊሰጧት በሽታ : ያንን ደህንነቷን የቀራትን ሀብቷን : እብደቷን ሊሰርቁ መላእክት ሰልፍ ያዙ : ጤንነት ሊያጠምቁ ምናለ ብትተዋት : እንዲህ ባትሻሙ "አዲሱ በሽታ : ጤንነት ነው ስሙ" (ብሏል ያ ገጣሚ ቢኖር ኖሮ ሰሚ). አለሁላት እኔ : መስካሪ ንፅህቷን እሷን ሲያጨልሙ : ሌሎቹን ማብራቷን ከራሷ እንኳ ሸሽታ : ብቻዋን ማንባቷን ነፍሷን አሳብዳ : ስጋዋን መክዳቷን ሞታም ኗሪነቷን ይዘምራል ቀሚስ ባበደ ገመድ ላይ ያላበደ ንፋስ የሚወዘውዘው ጥላሸት ያጠላት... አንዲት የጠቆረች... እብድ የተሰኘች... እስከምታነሳው።።።። በአቤኒ የተፃፈ ከወደዱት ለወዳጆ ያጋሩ @bewketuseyoum19 @bewketuseyoum19 1.4K views10:22