Get Mystery Box with random crypto!

የመኖር አካፋይ የመሞት ሲሶ መንገድ መሃል........ (ሜሪ ፈለቀ) ክፍል 17 | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

የመኖር አካፋይ የመሞት ሲሶ መንገድ መሃል........


(ሜሪ ፈለቀ)

ክፍል 17

የምጣደፈው ጎንጥን ሽሽት ይሆን ኪዳንጋ ለመድረስ ተቻኩዬ ወይም በሁለቱም ምክንያት የታክሲው ሹፌር ትዕግስቱን እስኪያንጠፈጥፍ ድረስ አቻኩለው ጀመር። <ምን ያህል ቀረን?> ፤ <ትንሽ ፈጠን ማለት አትችልም?> ፤ < ሌላ ያልተዘጋጋ አማራጭ መንገድ አይኖርም?> ፤ < አሁንም ብዙ ይቀረናል?> አንድ አይነት ጥያቄ በየሁለት ደቂቃው እየደጋገምኩ ፤ ግማሽ ጎኔ ወደፊት ግማሽ ጎኔ ወደኋላ በሆነ አቀማመጥ ፤ በአንድ ዓይኔ ወደኪዳን (ወደፊት) በአንድ ዓይኔ ወደጎንጥ (ወደኋላ) ሳማትር

«ሴትዮ ካልሆነ ውረጂ እና ሌላ ታክሲ ተሳፈሪ! አይታይሽም እንዴ በማይነዳበት እየነዳሁልሽ? ሆ! ዛሬ ምኗን ነው የጣለብኝ ባካችሁ?» አለ ያለመታከት ሲመልስልኝ ቆይቶ ከትዕግስቱ በላይ ስሆንበት

«ይቅርታ በጣም ስለቸኮልኩ ነው። ይቅርታ በቃ እንደሚመችህ አድርገህ ንዳ!!» አልኩኝ። ታክሲው ውስጥ በቦርሳ የያዝኩትን የቱታ ሱሪ ከቀሚሴ ስር ለብሼ ሳበቃ ቀሚሴን አውልቄ ወደቦርሳው ከተትኩ።

እያደረግኩት ያለሁት ድፍረት ይሁን ድድብና መመዘን የምችልበት መረጋጋት ላይ አልነበርኩም። ምናልባት አለማወቅ ደፋር ያደርግ ይሆናል ወይም ደደብ!! ጎንጥ ሰዎቹን ስለሚያውቃቸው ይሆናል የሚጠነቀቀው እና የሚፈራልኝ። የማላውቀውን ሰው ወይም ልገምት የማልችለውን የሚገጥመኝን ነገር በምነኛው መጠን ልፈራ እችላለሁ? እስከገባኝ ድረስ ቢያንስ አለማወቄ ጎንጥን እስከአለመከተል ድረስ ደፋር ወይም አላዋቂ አድርጎኛል።

የተባለው ቦታ ስደርስ ለቀጠሯችን 20 ደቂቃ ይቀረኛል። ከታክሲው ከወረድኩ በኋላ እንደማንኛውም በአካባቢው እንዳለ ተንቀሳቃሽ ግለሰብ የአዘቦት ክንውን እየከወንኩ ለመምሰል ጣርኩ እንጂ እንደሌባ ዓይኖቼም አካሌም እየተቅበጠበጠ ነበር። እስከዚህ ደቂቃ ያልተሰማኝ ፍርሃት አጥንቴ ድረስ ዘልቆ ይገለባበጥ ጀመር። መቆምም መራመድም መቀመጥም ሰው ይቸግረዋል? ወደላይ ትንሽ ራመድ እልና ደግሞ በተቃራኒው አቅጣጫ እመለሳለሁ። በመሃል እንደማቅለሽለሽም ያደርገኝና መሃል የእግረኛ መንገድ ላይ ቁጢጥ እላለሁ። ከመንበጭበጬ ብዛት ሽንቴን እላዬ ላይ የምለቀው መሰለኝ። ሰዓቴን በ60 ሰከንድ ውስጥ 120 ጊዜ አያለሁ። ደቂቃው ሰዓቴ መስራቱን ያቆመ ይመስል ፈቅ አይልም። ለአፍታ የጎንጥ እጅ ናፈቀኝ። ወላ ተከትሎ ደርሶብኝ በሆነና የፈራሁ ሲመስለው ሁሌም እንደሚያደርገው በዛ ሰፊ መዳፉ እጄን አፈፍ አድርጎ እጁ ውስጥ ቢደብቀው። «……. እኔ የት ሄጄ? …… ማን አባቱንስ እና ነው? » ቢለኝ። ሜላት ምንድነው ያደረግሽው?

የምጠብቀው እንዲህ ነበር። የሆነ ቀን እንዳየሁት የሆነ ፊልም። ጥቁር መኪና መጥቶ አጠገቤ ገጭ ብሎ ይቆምና ! በሩ ብርግድግድ ብሎ በተጠና ስልት ሲከፋፈት ፊታቸው የማይታዩ መሳሪያ የታጠቁ ግባብዳ ሰዎች ከመኪናው ዱብ ዱብ ብለው ያስቀመጡትን የሆነ ሻንጣ ብድግ እንደማድረግ ብድግ አድርገውኝ እየጮህኩ እግሬ አየር ላይ ተንጠልጥሎ ስፈራገጥ ምንም ሳይመስላቸው ወደመኪናው ይወረውሩኝና ልክ እንደቅድሙ በተጠና መንገድ በሩን ድው ድው አድርገው ዘጋግተው ይዘውኝ ይሄዳሉ።

የሆነው እንዲህ ነው። እግሬን ብርክ ይዞት ጉልበቴን ደገፍ ብዬ ባጎነበስኩበት አንዲት ቆንጅዬ ጅንስ ሱሪ በቲሸርት ለብሳ አጭር ጥቁር ጃኬት የደረበች ወጣት ሴት ከጀርባዬ ጠራችኝ። «ሜላት!» ለሰላምታ እጇን ዘረጋችልኝ። እነሱማ ሰላም ሊሉኝ አይችሉም ብዬ እያሰብኩ እጄን ዘረጋሁ!!

«ዝግጁ ነሽ?» ስትለኝ ማሰቢያዬ ተዛባ! ለምኑ ነው የምዘጋጀው? ለመታገት ዝግጅት? <አዎ! እጄን ለካቴና በቅባት አሸት አሸት አድርጌ አዘጋጅቸዋለሁ። ድንገት እጃችሁ ካረፈብኝ ዱላ መቻያ ደንደን እንዲል ቆዳዬን ወጠርጠር አድርጌ አለማምጄላችኋለሁ….. > እንድላት ነው ተዘጋጀሽ የምትለኝ? እሷ ቀጠል አድርጋ ከፊቴ ወደቆመ ዘናጭ ነጭ መኪና እየጠቆመችኝ ፈገግታዋ የሆነ የተንኮል ዓይነት እየሆነ « …. ግርግር አንፈልግም አይደል?» ብላ አጭሩን ጃኬቷን ከፈት አድርጋ ሽጉጧን አሳየችኝ። ለስሙማ እኔምኮ ሽጉጤን ጎኔ ላይ ሽጬዋለሁ። ምን ላደርግበት እንደሆነ ያሰብኩት ባይኖርም ለዝህች በቆንጆ ፊቷ ለሸወደችኝ ልጅ ግን ሽጉጥ ሳይሆን የመዘዝኩት እጄን ነው ለሰላምታ የዘረጋሁት።

ወዳሳየችኝ መኪና ሄድኩ። እያገተችኝ ሳይሆን የሆነ በክብር እንግድነት የተጠራሁበት ቦታ ልታደርሰኝ ነው የሚመስለው። የኋላውን በር ከፍታ ያንን ተንኮለኛ ፈገግታዋን እያሳየችኝ እንድገባ ጋበዘችኝ። በአጠገባችን የሚያልፉ ሰዎችን <ኸረ በትኩረት ለአፍታ እዩኝ እየወሰዱኝ ነው!> ብል ደስ ባለኝ። ማንም ለአፍታ እንኳን ገልመጥ አድርጎ ያየኝ የለም። በየእለት ተእለት ውሏችን ልብ ያላልናቸው ስንቶች ይሆኑ ከአይናችን ስር ብዙ የሆኑት?

መኪና ውስጥ ከኋላ ታግቼ ባይሆን « ምን ሆኖ ነው እንዲህ የቆነጀው?» የምለው የሚመስለኝ ፈርጣማ ወንድ ተቀምጧል። እንደገባሁ ቀለበኝ ማለት ይቀላል። ፓንቴ ስር መግባት እስኪቀረው እንያንቀረቀበ ሲፈትሸኝ ልጅቷ ከፊት ወንበር ሆና ሽጉጧን አስተካክላ ትጠብቀቃለች። የምራቸውን ነው? እዝህች የክብሪት ቀፎ የምታክል መኪናቸው ውስጥ ከነሹፌሩ ለሶስት ከበውኝ ታጠቃናለች ብለው ነው ሽጉጡ? ሽጉጤን ከፊት ለተቀመጠችው ሴት እንደመወርወር አድርጎ አቀብሏት በምትኩ የሆነ ጨርቅ ስትወረውርለት ነገረ እቅዴ ሁሉ ጎንጥ እንዳለው የጅል መሆኑ ገባኝ። የሰውየው መዋከብ ቶሎ የመጨረስ ውድድር ያለበት ነው የሚመስለው። በጨርቁ ዓይኔን ሲሸፍነው መኪናው መንቀሳቀስ ጀመረ። በዚያው ፍጥነት እጄ ላይ ካቴና አሰረ።

ለምን ያህል ደቂቃ እንደተጓዝን አላውቅም!! ወይ ከላይ ወይ ከታች እንዳያመልጠኝ ከሰውነቴ ጋር ግብ ግብ ላይ ነበርኩ። የእነርሱ ዝምታ ደግሞ ጭራሽ ያለሁት መኪና ውስጥ ሳይሆን ከሞት በኋላ የሰይጣን ፍርድ ዙፋን ስር ቀርቤ አስፈሪ ፍርድ ለምሳሌ እንደ < ለእሷ እሳቱ አስር እጥፍ ይጨመር!! ይሄማ ለሷ ሻወር መውሰጃዋ ነው!! ይንተክተክላት ውሃው እንጂ! > የሚል ፍርድ እየተጠባበቅኩ መሰለኝ። ከመኪናው ወርደን የበረበረኝ ሰውዬ ይመስለኛል ብብቴ ስር ገብቶ ጨምቆ ይዞኝ እየነዳኝ በእግር የሆነ ያህል እንደተጓዝን አይኔን የሸፈነኝ ጨርቅ ሲነሳ የተንጣለለ በውብ እቃዎች የተሞላ ሳሎን ራሴን አገኘሁት። ያሰረልኝ ሰውዬ ከእጄ ላይ ካቴናውን አወለቀው።

እንግድነት የሄድኩ ይመስል እንድቀመጥ ታዘዝኩ። ያ ሰውዬ በቪዲዮ ያወራሁት ሰውዬ እና አንዲት መሬቱን የነካ ጌጠኛ ቀይ ቀሚስ የለበሰች ሴት ተቀምጠዋል። ከእነርሱ በተጨማሪ ይዞኝ የገባው ሰውዬ እና ትንሽ ቁመቱ አጠር ያለ መሳሪያ የታጠቀ ሰውዬ ብቻ ናቸው ክፍሉ ውስጥ ያሉት። ሴትየዋ የጠቆመችኝ ከፊታቸው ያለ ሶፋ ላይ ለመቀመጥ ቂጤን ሳሾል «ከመጨዋወታችን በፊት እንዳው ለመተማመኑ …..