Get Mystery Box with random crypto!

ኢትዮጵያ እስከተያዘው የጎርጎርሳውያኑ 2021 መጨረሻ አንድ አምስተኛውን ህዝቧን የኮቪድ 19 ክትባ | DW Amharic

ኢትዮጵያ እስከተያዘው የጎርጎርሳውያኑ 2021 መጨረሻ አንድ አምስተኛውን ህዝቧን የኮቪድ 19 ክትባት ለመከተብ ዝግጅት እያደረገች መሆኗን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ እንዳለው እስከ የፊታችን ሚያዝያ ወር የምትረከበውን 9 ሚሊዮን ጸረ ተህዋሲውን ክትባት ማዘዟን ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል። በዚህም እስከ የጎርጎርሳውያኑ የ2021 መጨረሻ ድረስ 20 በመቶ የሚሆነውን የሕብረተሰብ ክፍል ክትባቱን ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ሚኒስትሯ ለሮይተርስ የዜና ምንጭ ገልጸዋል። ሀገሪቱ «የጸረ ተህዋሲውን ክትባት በእርዳታ ማግኘት በሚያስችላት ሁኔታ ላይ ስትሰራ ነበር» ያሉት ሚንስትሯ ነገር ግን ክትባቱን ኮቫክስ በተባለው እና ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በመሆን ደሃ ሀገራት ክትባቱን በፍትሃዊነት እንዲያገኙ በሚሰራ ጥምረት በኩል በኩል ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ነገር ግን በኮቫክስ በኩል ይቀርባል የተባለው ክትባት የትኛው እንደሆነ ዶ/ር ሊያ ያሉት ነገር የለም ። ኢትዮጵያ የጸረ ተህዋሲውን ክትባት በግዢ ለማቅረብ 328 ሚሊዮን ዶላር ወይም 13 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልጋት መንግስታዊው የዜና ምንጭ ኢዜአ ዘግቧል። በኢትዮጵያ 142,000 ሰዎች በኮሮና ሲያዙ 2100 የሚሆኑት ደግሞ ከኮሮና ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን አጥተዋል። የተቀረው ዓለም ክትባቱን በዘመቻ መስጠት በጀመረበት በዚህ ጊዜ አፍሪቃ 1,3 ቢሊዮን ለሚሆነው ህዝቧ ክትባቱን ለማድረስ ብርቱ ጥረት ይጠይቃታል ተብሏል። በአህጉሪቱ የተሻለ አቅም ያላቸው ብቻ ክትባቱን ማግኘት መጀመራቸውን ዘገባው አመልክቷል።