Get Mystery Box with random crypto!

ዜናው በዝርዝር *የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) 25 ተጨማሪ ሠራተኞቹ ትግራይ ክልል ውስ | DW Amharic

ዜናው በዝርዝር

*የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) 25 ተጨማሪ ሠራተኞቹ ትግራይ ክልል ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ፍቃድ ማግኘቱን ዐስታወቀ።ፈቃዱን አስመልክቶም፦ የዓለም አቀፍ ድርጅት ዋና ፀሐፊ የአንቶኒዮ ጉተሬሽ ቃል አቀባይ ሽቴፋን ዱዦሪክ፦ የርዳታ ሠራተኞች ትግራይ ክልል ውስጥ በተቀላጠፈ መልኩ ርዳታ ማቅረብ እንዲችሉ «የመጀመሪያው ርምጃ ነው» ብሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ያከናወናቸውን ቀና ያሉትን ቊርጠኝነት ቃል አአቀባዩ በመግለጫቸው አውስተዋል። በአሁኑ ወቅት 60 የሚጠጉ የተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሰብአዊ ድጋፍ አቅራቢ ሠራተኞች ወደ ትግራይ ለመንቀሳቀስ አዲስ አበባ ሆነው እንደሚጠብቊም ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል። የዓለም ምግብ ድርጅት (WFP)የኢትዮጵያ መንግሥት፦ «ወደ ትግራይ የሚገቡ እና የሚሠራጩ የርዳታ ጭነቶችን» በተመለከተ «ባለሥልጣናቱን እና የርዳታ ድርጅቶቹን ለማገዝ» አቀረበ ያለውን ጥያቄም መቀበሉንም ዐስታውቀዋል። ከዚያም ባሻገር የዓለም ምግብ ድርጅቱ እስከ አንድ ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች ትግራይ ውስጥ አስቸኳይ የምግብ ርዳታ ለማቅረብ መስማማቱንም ጠቊመዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተጨማሪ ሠራተኞች ፈቃድ መስጠቱን አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፦ መንግሥት ቃሉን እንዲጠብቅ ጠይቋል። የኢትዮጵያ መንግሥት እና አጋሮቹ ቀደም ሲል 1,8 ሚሊዮን ለሚጠጋ ነዋሪ ትግራይ ውስጥ ርዳታ ማድረሳቸውን የዓለም ምግብ ድርጅት ኃላፊ ዳቪድ ቤያስሌይ ማወደሳቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንሥቴር ዛሬ በሰጠው ሳምንታዊ መግለጫ ገልጧል። በሁለት የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ 26,000 ኤርትራውያን ስደተኞችም የምግብ ርዳታ እና የአልሚ ምግብ እንደታደላቸው አክሎ ጠቅሷል።

*ሦስት የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽነሮች ትናንት በጋራ ባወጡት መግለጫ፦ ትግራይ ክልል ውስጥ ግጭት እያባባሱ የሚገኙ ያሏቸው የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ጥሪ አቀረቡ።ዩናይትድ ስቴትስ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ እንዲወጡ ከዚሕ ቀደም ያደረገችዉን ጥሪ ሕብረቱ እንደሚደግፍ ኮሚሽነሮቹ አስታዉቀዋል። የኤርትራ ወታደሮች ግፍ ይፈጽማሉ፣ ግጭት እና ኹከት እንዲባባስም ሰበብ ሆነዋል ብሏል የኅብረቱ ሦስት ኮሚሽነሮች የጋራ መግለጫ። መግለጫውን የሰጡት የኅብረቱ የውጭ ግንኙነት ኃላፊና የኮሚሽኑ ምክትል ፕሬዚደንት ጆሴፍ ቦሬል፤ የአስቸኳይ ርዳታ ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺች እና የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነሯ ጁታ ኡርፒላይነን ናቸው።ትግራይ ክልል ውስጥ እየታየ ያለው «አስከፊ» የሰብአዊ ቀውስ እና በአካባቢው ሊያደርስ የሚችለው ተጽዕኖ ያሳሰባቸው መሆኑን አክለው ገልጠዋል። የሰብአዊ ርዳታው መዳረስ በትግራይ ክልል እና በአጎራባች አካባቢዎች የአፋር እና የአማራ ክልሎችም የሰብአዊነት መርኆችን፣ ገለልተኝነትን፣ ሰብአዊነትን፣ ለማንም ባልወገነ እና ነጻ በሆነ መልኩ ሊረጋገጥ እና ሊፈቀድ ይገባል ብለዋል።

*የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ሠርጌ ላቭሮቭ፦ የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይ ክልል ውስጥ የሰብአዊ ተግዳሮትን ለመወጣት የሚያደርገውን ጥረት የሩስያ ፌዴሬሽን ዕውቅና እንደሚሰጥ ገለጡ። የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ይህን ያሉት ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ እና ምክትል ሚንሥትር ደመቀ መኮንን ጋር ትናንት በስልክ ከተወያዩ በኋላ ነው። በውይይቱ ወቅትም አቶ ደመቀ በትግራይ ክልል ውስጥ ስላለው መልሶ ግንባታ እና ማቋቋም ለሠርጌ ላቭሮቭ ማብራራታቸው ተጠቊሟል። ትግራይ ውስጥ የሰብአዊ ድጋፍ ኹኔታ ስኬታማ በሆነ መልኩ መቀጠሉን ማብራራታቸውንም ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ገልጧል። ሠርጌ ላቭሮቭ የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን የሰብአዊ ተግዳሮትን በተመለከተ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚረዱ መንግሥታቸውም በዚህ ጉዳይ ኢትዮጵያን መርዳቱን ለመቀጠል ምንጊዜም ዝግጁ መሆኑን ጠቊመዋል። ሩስያ አባል የሆነችበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት በትግራይ ጉዳይ በዝግ መምከሩ የሚታወስ ነው።

*ኢትዮጵያ እስከ ሚያዝያ ወር ድረስ 9 ሚሊዮን የኮሮና ተሐዋሲ መከላከያ ክትባት ብልቃጦችን ለማስገባት ማቀዷ ተገለጠ። የትኞቹ አይነት ክትባቶች እንደሆኑ ግን አለመገለጡን ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል። ኢትዮጵያ ክትባቶቹን ለማስገባት ግዢ የፈጸመችው በቀጥታ ሳይሆን ክትባቶችን ለሁሉም ሃገራት ለማዳረስ የዓለም ጤና ድርጅት እና አጋሮቹ በተቋቋመው ኮቫክስ ከተሰኘው ተቋም መሆኑም ተጠቅሷል። ኮቫክስ በጣምራ የሚመራው ደሃ ሃገራት ክትባቶች እንዲዳረሣቸው ይንቀሳቀሳል በተባለው ጋቪ ጥምረት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ከ142 ሺህ በላይ ሰዎች ተመርምረው 2,154 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን የጤና ሚንሥትር መረጃ ይጠቊማል። ኮቫክስ ክትባት አቅራቢ ተቋም በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ቢያንስ 330 ሚሊዮን የክትባት ብልቃጦችን ለደሃ ሃገራት ለማቅረብ አቅዷል። ለደሃ ሃገራት ይቀርባሉ ከተባሉት የክትባት ብልቃጦች መካከል 240 ሚሊዮን የሚደርሰው የህንድ ተቋም ከሚያመርተው አስትራዜኔካ-ኦክስፎርድ የሚገኝ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል። ቀሪው 96 ሚሊዮን ከአስትራዜኔካ መሆኑ ተጠቊሟል። አውራፓውያን የሚረባረቡበት ፕፋይዘር ባዮንቴክ ክትባት ግን 1,2 ሚሊዮን ብቻ ነው ለድሃ ሃገራት ሊሰጥ የታሰበው። ደቡብ አፍሪቃ አስትራዜንካ ስተባለዉ የኮሮና መከላከያ ክትባት ዝርዝር መረጃ እስከምታገኝ ክትባቱን ጥቅም ላይ እንደማታዉል መግለጿ ትናንት ተዘግቧል።

*በደብረ ማርቆስ ከተማ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ 10 የሚሆኑ የሉካንዳ ቤቶች መቃጠላቸውን የከተማይቱ ፖሊስ አስታወቀ፡፡ የፖሊስ ጽ/ቤቱ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አጃናው አዲስ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ከንጋቱ 12 ሠዓት ተኩል አካባቢ በከተማዋ ቀበሌ 01 በተነሳው ቃጠሎ 10 ሉካንዳ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡ እሳቱ ወደሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋ የከተማው ወጣቶች ተቆጣጥረውታል ብለዋል፡፡ የጉዳቱ መጠን እየተጠና ሲሆን በቅርቡም በተመሳሳይ ሁኔታ በከተመው የሸቀጦች መሸጫ ላይ ቃጠሎ ተከስቶ ከ20 በላይ አነስተኛ ሱቆች ከነንብረታቸው መውደማቸውን አስታውሰዋል።

*ምሥራቅ አፍሪቃን ከዚህ ቀደም ከታየው የበረታ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ሊያጠቃት እንደሚችል ጀርመን አኸን ከተማ የሚገኘው ሚዜሬዎር የተሰኘው የርዳታ ተቋም አስጠነቀቀ። ከአንድ ዓመት በፊት ከታየው የባሰ ነው የተባለለት ሁለተኛ ዙሩ መጠነ ሰፊ የበረሃ አንበጣ መንጋ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኬንያ ውስጥ ከፍተኛ የሰብል ጥፋት ሊያደርስ መሆኑ አሳስቦኛል ብሏል ርዳታ ድርጅቱ። መንጋው ከፍተኛ የሰብል ጥፋት አድርሶ ረሐብ ሊቀሰቅስም ይችላል ሲል ሚዜሬዎር አስጠንቅቋል። የኦለም ምግብ ድርጅት (FAO) በበኩሉ የበረሃ አንበጣ መንጋው ወደ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ እና ጅቡቲ ድረስ ሊሠራጭ ይችላልም ብሏል።