Get Mystery Box with random crypto!

የአውሮጳ ህብረት ማዕቀብ የሚጥልባት ከሆነ ግንኙነቷን ልታቋርጥ እንደምትችል ሩስያ አስጠነቀቀች። ሩ | DW Amharic

የአውሮጳ ህብረት ማዕቀብ የሚጥልባት ከሆነ ግንኙነቷን ልታቋርጥ እንደምትችል ሩስያ አስጠነቀቀች። ሩስያ ማስጠንቀቂያውን የሰጠችው ምዕራባውያኑ በአሌክስ ናቫልኒ መታሰር በሩስያ ላይ ማዕቀብ ከጣሉ ሩስያ ከሕብረቱ ጋር የሚኖራትን ግንኙነት ልታቋርጥ እንደምትችል የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ስርጌይ ላቭሮቭ ተናግረዋል። ላቭሮቭ ዛሬ በቴሌግራም በሚተላለፍ አንድ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ «ከሕብረቱ ጋር ግንኙነት ታቋርጡ ይሆን» ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ »ሕብረቱ የሩስያን ኢኮኖሚ ሊጎዳ የሚችል የማዕቀብ እርምጃ ከወሰደ ሩስያም በበኩሏ የራሷን እርምጃ ትወስዳለች » ሲሉ ተደምጠዋል። « ለዚያ ደግሞ ዝግጁ መሆናችንን እንቀጥላለን» ብለዋል ላቭሮቭ ፡፡ ከዓለማቀፍ ግንኙነት ራሳችንን መነጠል አንፈልግም ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ «ነገር ግን ለዚያ ዝግጁ መሆን ይኖርብናል ፤ «ሰላም ከፈለክ ለጦርነት ተዘጋጅ» የሚል አባባል ለንግግራቸው ተጠቅመዋል፡፡የህብረቱ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን በበኩላቸው ሩስያ ለብቻዋ ለመነጠል እና ምዕራባውያንን ለመከፋፈል እየጣረች ነው ሲሉ ወቅሰዋል። በአውሮፓ ህብረት የሩሲያ ተወካይ ቭላድሚር ቺዝሆቭ ቀደም ሲል ዛሬ አርብ ጥዋት በኢዝቬሺያ ጋዜጣ ላይ በተለይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሩሲያ እና የአውሮፓ ህብረት ውይይቶች እንደሚቀጥሉ እና የቦረል ወደ ሞስኮ ለመጓዝ ፈቃደኛ መሆናቸው ነገሮች መስመር እንዳይለቁ ለማድረግ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል ፡፡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ጀርመን እና ፈረንሳይ ይሁንታቸውን ከሰጡ በኋላ የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አጋሮች ላይ የጉዞ እቀባ እና የንብረት እገዳ ለመጣል አቅዷል ፡፡