🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሠራዊት የመንግሥት ኃይሎች በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍተ | DW Amharic

የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሠራዊት የመንግሥት ኃይሎች በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍተውብኛል አለ። የቡድኑ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ በትዊተር ገጻቸው ያጋሩት የቡድኑ መግለጫ፤ የታንዛኒያው የሰላም ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ በበርካታ አካባቢዎች የመንግሥት ኃይሎች ጥቃት እንደከፈቱበት አመልክቷል። እንዲህ ያለው እርምጃም በሰላም ውይይቱ ግጭትን ለመቀነስ የተደረሰባቸውን የመግባቢያ ሃሳቦች በእጅጉ የሚጻረር ነው ብሏል። ቡድኑ ለሰላም ካለው ቁርጠኝነት ባሻገርም በምዕራብ ወለጋ፣ በምሥራቅ ወለጋ፤ በሆሮ ጉድሩ፤ በምዕራብ ሸዋ፣ በምሥራቅ ሸዋ፣ በአርሲ፣ በሐረርጌ፣ ቦረና እና ጉጂ ይዞታዎቹን ለመከላከል መገደዱንም አመልክቷል። ቡድኑ በመግለጫው አክሎም በአሁኑ ጊዜ የተከፈተበትን ጥቃትም ለሁለተኛው ዙር ውይይት የበላይነት ይዞ ለመቅረብ ያለመ ነው ብሎታል።እንዲያም ሆኖ በመንግሥትና በቡድኑ መካከል ሁለተኛ ዙር ውይይት መቼ እንደሚካሄድ በመግለጫው አልተጠቀሰም። ታጣቂው ቡድን ያሰማውን ክስ በተመለከተ ከመንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም። እንዲያም ሆኖ የመንግሥት እና የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሠራዊት ኃይሎች በሚፋለሙባቸው የተጠቀሱት አካባቢዎች ነዋሪዎች በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኙ የሚያመላክቱ ዘገባዎች እየወጡ ነው።