Get Mystery Box with random crypto!

ካዳስተር ማለት ምን ማለት ነው? ካዳስተር ማለት የመሬት ይዞታን መሰረት ያደረገ የመሬት መረጃ ሥ | Corporate Lawyer

ካዳስተር ማለት ምን ማለት ነው?

ካዳስተር ማለት የመሬት ይዞታን መሰረት ያደረገ የመሬት መረጃ ሥርዓት ሲሆን የሚደራጁት መረጃዎችም በዋናነት ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡

እነዝህም

አንደኛው የካርታ መረጃ (spatial data) የይዞታውን መገኛ ቦታ፣ ወሰኑን፣ ስፋቱንና ቅርፁን፣ አጎራባች ይዞታዎችን እና አዋሳኝ መንገዶችን የሚያሳይ ሲሆን

ሁለተኛው ገላጭ መረጃ (non-spatial data) በመባል የሚታወቀው የባለይዞታውን ማንነት (ስም፣ አድራሻ፣ ጾታ፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ ወዘተ)፣ በይዞታው ላይ ያለው መብት፣ ክልከላና ኃላፊነት፣ የቦታው አገልግሎትና ደረጃ፣ ወዘተ… እንደ ካዳስተር ዓይነቱ ተዘርዝረው የሚያዙ መረጃዎችን ያካትታል፡፡

እነዚህ ሁለት የመረጃ ዓይነቶችም በልዩ የይዞታ መለያ ኮድ እንዲገናኙ ይደረጋል፡፡

ካዳስተር በሦስት ዓይነት ይከፈላል፡-

አንደኛው:- ህጋዊ ካዳስተር ሲሆን ለእያንዳንዱ ህጋዊ ወሰን ለተለየለት ይዞታ፣ የይዞታ መብት፣ ክልከላና ኃላፊነት የሚያመለክት መረጃ ከይዞታው ካርታ ጋር አጣምሮ የያዘ ወቅታዊ የመሬት ይዞታ መረጃ ሥርዓት ሲሆን አስፈላጊነቱም የትኛው ይዞታ በማንና በምን አግባብ ተይዟል የሚለውን በማጣራት የባለይዞታውን የይዞታ ዋስትና ለማረጋገጥ ነው፡፡

ሁለተኛው ዓይነት ፊስካል ካዳስተር ሲሆን በይዞታው ላይ ስላረፈው ቋሚ ንብረት ዝርዝር መረጃ እና የመሬቱን ወቅታዊ ግምት ከይዞታው ካርታ ጋር የሚይዝ ሆኖ ለቦታና ለንብረት ግብር ክፍያ የሚያገለግል ሥርዓት ነው፡፡

ሦስተኛው ሁለገብ/ሁሉን አቀፍ ካዳስተር/ የሚባለው በሁለቱ የካዳስተር ዓይነቶች የተገለፁትን መረጃዎች የሚይዝ ሆኖ በተጨማሪም የመሰረተ ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ሌሎች መረጃዎችን እና ካርታን አካቶ የሚይዝ የመረጃ ሥርዓት ነው፡፡

የህጋዊ ካዳስተር ዝርጋታ ተግባራዊ መሆን የሚያስገኛቸው ፋይዳዎች

* በዘርፉ በመረጃ አያያዝ ጉድለት የነበረውን ችግር ተጠቅመው ጥቂቶች አላግባብ የሚበለፅጉበትንና ህጋዊ ባለይዞታዎችን ለተለያዩ ጉዳቶች ይዳርግ የነበረውን የአሰራር ችግር ሊፈታ ይችላል ተብሎ ይታመናል።

* የከተማ አስተዳደሮች የሚያስተዳድሩትን መሬት ቆጥረው እንዲያውቁ፣ የትኛውን መሬት ለየትኛው አገልግሎት ማዋል እንዳለባቸው አቅደው እንዲሰሩና በተገቢው መንገድ እንዲያስተዳድሩ ከፍተኛ እገዛ ያደርግላቸዋል።

* ከተሞች ከመሬት ሃብታቸው መሰብሰብ የሚገባቸውን ግብር እና ኪራይ በተገቢው መንገድ በመሰብሰብ ለከተማው የመሰረተ-ልማት ግንባታ በማዋል ከተሞች በስርአቱ ያድጋሉ፣ የከተማው ነዋሪም የልማቱ ተጠቃሚ ይሆናል።

* የካዳስተር ስርዓቱ በሚፈጥረው የመረጃ ምልዑነት በከተማ መሬት ይዞታ የሚስተዋለውን በዜጎች መካከል የሚፈጠረውን ክርክር ይቀንሳል፣ በዚህ ምክንያት የሚያጠፋውን ገንዝብ፣ ጊዜ እና የፍትህ መጓደል ይቀንሳል።

* ማንኛውም ዜጋ በከተማ መሬት ይዞታ ዘርፍ ማግኘት የሚፈልገውን መረጃ ብዙ ውጣ ውረድ ሳይገጥመው በቀላሉ እንዲያገኝ ያደርጋል።
ጽሁፍ:- የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር