Get Mystery Box with random crypto!

ስለ መድን ውል- የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም ======================== የመድን ውል | Corporate Lawyer

ስለ መድን ውል- የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም
========================
የመድን ውል አመሰራረትና አፈጻጸምን አስመልክቶ የሰበር ችሎት በበርካታ መዝገቦች የህግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በከፊሎቹ ላይ የተሰጠው የህግ ትርጉም እና የህግ ትንተና እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

1. የመድን ውል አመሰራረት

የመድን ውል ሲመሰረት እንደማንኛውም የውል አቀራረብና አቀባበል /offer and acceptance/ ሊኖር የሚገባ ሲሆን የውል አቀባበል /offer/ የሚከናወነው ደግሞ መድን ገቢው በመድን ሰጭው የሚዘጋጅን መግለጫ /proposal form/ ሲሞላና ይህንኑ መግለጫም ለመድን ሰጭው ሲያስረክብ ነው፡፡ በመድን ገቢው የቀረበው የውል አቀራረብ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል ለማለት የሚቻለው ደግሞ መድን ሰጭው በተዘጋጀው ፖሊሲ ላይ በሚፈርምበት ጊዜ /The issuance of policy/ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በሁለቱ ወገኖች መካከል የመድን ውል የተቋቋመ በመሆኑ የትኛውም ወገን ሊያቋርጠው አይችልም፡፡

መድን ሰጪው በሚያዘጋጀው ፖሊሲ ላይ መድን ሰጭው መፈረም እንዳለበት በን/ህ/ቁ. 657 ከመመልከቱ በስተቀር መድን ገቢው መፈረም እንደሚገባው ያልተመለከተ በመሆኑ በውል ማቅረቢያ /offer/ ሰነዱ ላይ መድን ገቢው ከፈረመና በፖሊሲው ላይ ደግሞ መድን ሰጭው ከፈረመ በሁለቱ መካከል የመድን ውል ስለመደረጉ በቂ አስረጂ እንደሆነ ከንግድ ህጉ አኳያ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 24703 ቅጽ 7፣[1] ሰ/መ/ቁ 78180 ቅጽ 15፣[2] ን/ህ/ቁ. 651፣ 654፣ 657

2. የውሉ መሻሻል

የኢንሹራንስ ፖሊሲ ተጨማሪ በሆነ ጽሑፍ ካልሆነ በቀር ሊለወጥ እንደማይችል የን/ህ/ቁጥር 657(2) አስገዳጅነት ባለው መልኩ ደንግጓል፡፡ የዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር ሲታይም ፖሊሲው ወይም የፖሊሲው ተጨማሪ ጽሁፍ ከመፈረሙ በፊት ለጊዜው ኢንሹራንስ ሰጪው ኢንሹራንስ ለሚገባው ሰው ፖሊሲው ወይም ለፖሊሲው ተጨማሪ ጽሑፍ እስከ ተፈረመ ድረስ ማረጋገጫ መድን የሚሆነው ጽሑፍ የሠጠው እንደሆነ ኢንሹራንስ ሰጪውና ኢንሹራንስ ገቢው አንዱ ለአንዱ ግዴታ እንደገቡ ይቆጠራል በሚል ይደነግጋል፡፡ የዚህ ድንጋጌ አይነተኛ ዓላማም ውሉ ስለመኖሩ የሚረጋገጠው በጽሑፍ በሆነ ሰነድ መሆኑን ማሳየት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡

ሰ/መ/ቁ 78180 ቅጽ 15፣[3] ን/ህ/ቁ. 657(2)

3. የመድን ሰጪው ኃላፊነት

ኢንሹራንስ የተገባለት መኪና በህግ ከተፈቀደው ቁጥር በላይ ተሳፋሪዎች ጭኖ ሲጓዝ ለደረሰበት አደጋ መድን ገቢው የዋስትና ሽፋን ገንዘብ የመክፈል ግዴታ የለበትም፡፡

የንብረት ኢንሹራንስ ውል ከተለያዩ የውል አይነቶች አንዱ ሲሆን ውሉም ህጋዊ የሆኑ ተግባራት በሚከናወኑበት ጊዜ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በዋስትናው ሽፋኑ መሰረት ለመካስ በማሰብ ሊደረግ የሚገባ ነው፡፡ በፍ/ህ/ቁ. 1678 (ለ) እንደተመለከተው አንድ ውል በቂ የሆነ እርግጠኛነት ያለውና ህጋዊ የሆነ ጉዳይ ለማከናወን ሊደረግ ይገባል፡፡ ህጋዊ ውል የሚደረገው በህግ እንዲደረግ ያልተፈቀደውን ድርጊት ወይም የህግ ክልከላ የተደረገበትን ጉዳይ በማከናወን ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ወይም በሚኖረው ፍላጎት መነሻ ሊሆን አይገባም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 90793 ቅጽ 15፣[4] ፍ/ህ/ቁ. 1678

መድን የተገባለት ተሳቢ መኪና በሌላ ተሳቢ ከተቀየረ ተሳቢው ለሚደርስበት ሆነ ለሚያደርሰው ጉዳት ኢንሹራንስ ሰጭው ኃላፊነት የለበትም፡፡

ኢንሹራንስ ሰጭው በውሉ ለተመለከተው አደጋ ብቻ መድን ለገባው ሰው መድን እንደሚሆን በንግድ ሕግ ቁጥር 663 ንዑስ አንቀጽ 1 ተደንግጓል፡፡ እንደዚሁም ኢንሹራንስ ሰጭው በውሉ ውስጥ የተመለከተው አደጋ በደረሰ ጊዜ ወይም በውሉ የተስማሙበት ቀን በደረሰጊዜ የተስማሙበትን ገንዘብ የመክፈል ግዴታ እንዳለበትና ይህ ግዴታው በውለታው ከተጠቀሰው ሊበልጥ እንደማይችል “የኢንሹራንስ ሰጭው ግዴታ” በሚል ርዕስ ባለው በንግድ ሕግ ቁጥር 665 ተደንግጓል፡፡

ሰ/መ/ቁ 76977 ቅጽ 14፣ ን/ህ/ቁ. 663/1/፣ 665

መድን የተገባለት መኪና የሾፌሩ ረዳት መንጃ ፈቃድ ሳይኖረው የመኪናውን ቁልፍ ሰርቆ ሲያሽከረክር አደጋ ከደረሰ መድን ሰጪው ካሳ የመክፈል ኃላፊነት የለበትም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 50199 ቅጽ 12[5]

ለጭነት ተሽከርካሪ የመድን ሽፋን የሰጠ የኢንሹራንስ ድርጅት በመኪናው ላይ ተሳፍሮ ጉዳት ለደረሰበት ሰው ተጠያቂነት የለበትም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 42139 ቅጽ 9[6]

መድን ሰጪው እና መድን ገቢው ቀደም ብሎ የተደረገና ለረጅም ጊዜ ጸንቶ የቆየ የውል ግንኝኑነት ቢኖራቸውም አደጋው በደረሰበት ዕለት የመድን ውሉ በህጉ አግባብ ካልታደሰ መድን ሰጪው ካሳ የመክፈል ኃላፊነት ይቀርለታል፡፡

የንግድ ህግ ቁ. 666 ተፈጻሚ የሚሆነው የፀና የመድን ውል ኖሮ መድን ገቢው አረቦን ሳይከፍል ከቀረ ነው፡፡ በድንጋጌው መሰረት አረቦን አለመክፈል መድን ገቢውን ከተጠያቂነት አያድንም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 52910 ቅጽ 10፣ ን/ህ/ቁ. 666

4. የካሳው መጠን

የንብረት ኢንሹራንስ ሽፋን የተሰጠው ንብረት ሙሉ በሙሉ ከወደመ መድን ገቢው ሊያገኝ የሚችለው ካሳ ንብረቱ በወደመበት ጊዜ የነበረውን ዋጋ ነው፡፡ ይህም መድን ውሉ ላይ ከተመለከተው የገንዘብ መጠን ሊያንስ ይችላል፡፡

የንግድ ሕግ አንቀጽ 665 በአጠቃላይ ጉዳት ለመካስ ወይም ለመተካት እና ለሰዎች ኢንሹራንስ ላይ ተፈፃሚነት ያለው ጠቅላላ ድንጋጌ ሲሆን፣ በይዘቱ የመድን ሽፋን የሚሰጠው የኢንሹራንስ ኩባንያ ለመዴን ገቢው ወይም ለተጠቃሚው ሊከፍለው የሚችለው ወይም ሊከፍለው የሚገባው የኢንሹራንስ ገንዘብ በመድን ውሉ ከተገለፀው ልበልጥ የማይችል መሆኑን የሚያሣይ ነው፡፡

ንግድ ሕግ አንቀፅ 678 ስለ ንብረት የተደረገ ኢንሹራንስ ውል የሚኖረውን ውጤት በልዩ ሁኔታ የሚደነግግ የሕግ ድንጋጌ ነው፡፡ በመርሕ ደረጃ ለንብረት የሚሰጥ የኢንሹራንስ ሽፋን አደጋው በደረሰበት ጊዜ ንብረቱ የነበረውን ዋጋ የሚያካክስ መሆን እንዳለበት የሚደነግግ ነው፡፡ በንብረት የሚደረግ ኢንሹራንስ መሠረታዊ ዓላማው ንብረቱ በመጎዳቱ ወይም ንብረቱ በመውደሙ በባለንብረቱ ላይ የደረሰውን ኪሣራ ለመተካት ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 69966 ቅጽ 13፣[7] ሰ/መ/ቁ. 48698 ቅጽ 10፣[8] ን/ህ/ቁ. 665፣ 678

በሶስተኛ ወገኖች ላይ ለሚደርስ የአካል ወይም የሞት አደጋ የመድን ሽፋን የሰጠ የመድን ድርጅት በካሳ ረገድ የተጠያቂነት ወሰኑ በውሉ ላይ ከተመለከተው የገንዘብ መጠን ሊያልፍ አይችልም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 46808 ቅጽ 10፣[9] ን/ህ/ቁ. 665/2/

መድን ሰጪው በአደጋ ምክንያት ለታጣ ወይም ለተቋረጠ ጥቅም ካሳ የመክፈል ግዴታ ባይኖርበትም መድን የተገባለት ንብረት አደጋ ሲደርስበት ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ በመድን ውሉ መሰረት ግዴታውን ካልተወጣ በመድን ገቢው ላይ ለሚደርሰው ኪሳራ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሆኖም መድን ገቢው ኪሳራ የመቀነስ ተነጻጻሪ ግዴታ ያለበት በመሆኑ መድን ሰጪው ሊከፍል የሚገባው የካሳ መጠን መኪናውን ለማስጠገን ለሚያስፈልገው ጊዜ ለደረሰው ኪሳራ ብቻ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 47076 ቅጽ 12፣[10] ፍ/ህ/ቁ. 1790፣ 1791፣ 1802

5. ይርጋ

አረቦን እንዲከፈል የሚቀርብ ክስ በሁለት ዓመት ይታገዳል፡፡