Get Mystery Box with random crypto!

==የአእምሮ ጤና እክሎችን መረዳት ለምን ከበደን?== ሐምሌ6/2014ዓ.ም. የአእምሮ ጤና እክሎች | 21St C. Soul

==የአእምሮ ጤና እክሎችን መረዳት ለምን ከበደን?==
ሐምሌ6/2014ዓ.ም.

የአእምሮ ጤና እክሎች ለመለየት አስቸጋሪ ናቸው፡፡ እንደ እድል ሆኖ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስለ ብዙ የአእምሮ ጤና እክሎች ያለን ግንዛቤ በተወሰነ ደረጃ ጨምሯል። ነገር ግን በህይወት ዘመን ውስጥ በጣም ለተለመደው የጭንቀት ህመም ተጋላጭነታችን ጨምሯልን?
***
የአእምሮ ጤና እክል ካለባቸው ሰዎች መካከል ግማሾቹ 15 ዓመት ሳይሞላቸው እና ሌላ ሩብ ደግሞ 25 ዓመት ሳይሞላቸው እንደሚጀምር ይታወቃል፡፡ ነገር ግን እክሎቹን በቀላሉ ለይቶ እርዳታ ለማግኘት ያለን ንቃተ ህሊና ብዙ ይቀረዋል፡፡ ይህ በተለይ ለውስጣዊ አእምሮ ጤና እክሎች ተብለው ለሚጠሩት እንደ ጭንቀት ህመምና ድባቴ የተለመደ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ በቀላሉ የሚታዩ ወይም በቀጥታ የሚያስደነግጡ አይደሉም፣ እናም እነዚህ ችግሮች በጓደኞች እና በቤተሰብ እንደ ችግር ሊወሰዱ አይችሉም።
***
የጭንቀት ህመም
የጭንቀት ህመሞች የህይወታችን አካላት ከሆኑት የእለት ተእለት ፍርሃቶች ለመለየት አስቸጋሪ ናቸው፡፡ ብዙ ግለሰቦች ይህ የማያቋርጥ ስሜት በጣም ረጅም ጊዜ እንደቆየ ሲረዱ ጭንቀትን እንደ ስብዕናቸው ተቀብለው ይኖራሉ፡፡ በጭንቀት ምክንያት የሚፈጠረው አለመረጋጋት ብዙውን ጊዜ ሰዎች የሚፈልጓቸውን ነገሮች ማድረግ እንዲያቆሙ ያደርጋቸዋል ወይም ወደ ጎጂ መቋቋሚያ መንገዶች እንዲፈልጉ ይመራቸዋል። በጭንቀት ዙሪያ ሕይወታቸውን መገንባት ሊጀምሩ ይችላሉ፡፡ ከዚያም ዋናው ችግር ብዙውን ጊዜ በተፈጠሩት ሌሎች ትንንሽ ችግሮች ይሸፈናል፡፡ አንድ ሰው ለምሳሌ ለሱስ ህክምና ወይም ለሌላ ጤና ህክምና ወደ ሀኪም ሲሄድ የጭንቀት ህመምን እንደ መሰረታዊ ችግር ማግኘት የተለመደ ነው፡፡
***
ከዕውቅና በታች
የጭንቀት ህመሞች በቀላሉ ሳይታዩ መታለፍ መቻላቸው እና ከሚሰቃዩት መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ወደ ህክምና መምጣታቸው ይታወቃል። እኛ የማናውቀው ግን ይህ እውቅና ማነስ መቼ እንደጀመረ ነው። የህይወት በተለያዩ አስጨናቂ ሁኔታዎች መሞላት፣ ከጭንቀት ጋር ተላምዶ መኖር፣ የጭንቀት አስከፊ ውጤትን አለመረዳት፣ ለአእምሮ ጤና ያለን ቦታ ማነስ እንዲሁም ለአእምሮ ጤና አክል ተጠቂዎች ያለን የተሳሳተ አስተሳሰብ ለእነዚህ ህመሞች ዕውቅና እንዳንሰጥ አግዶናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የጭንቀት መታወክ ከህብረተሰብ እይታ አንጻር በጣም ዝቅ ያሉ ችግሮች መሆናቸው፣ ህብረተሰቡ ጭንቀት ምን ያህል የተስፋፋ እና የሚያዳክም እንደሆነ ጠንቅቆ አለመረዳት ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው፡፡
***
ግንዛቤ
አሁን ባለው የኮሮና ወረርሺኝ ወቅት እና የሀገራችን አለመረጋጋት በፍርሃት ውስጥ መኖር ምን ያህል ከባድ እና አስፈሪ እንደሆነ አሳይቶናል፡፡ ስውር ለሆነብን ችግርም ትልቅ አይን እንድናዳብር ይረዳናል። አሁን ያለንበት ጭንቀት የከፋ ደረጃ ሳይደርስ ዕርዳታ መጠየቅን፣ ስለ አእምሮ ጤና ያለንን ዕውቀት ማስፋትን፣ ለሰዎች ቀና መሆንን እና ህክምና ማግኘትን እንደ ባህል ማዳበር ይጠበቅብናል፡፡

ኢምፓክት ኢትዮጵያ
ሐምሌ 6/2014ዓ.ም