Get Mystery Box with random crypto!

#Update የቀድሞ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታን (ዶ/ር) ጨምሮ 15 ግለሰቦች ላይ | STUDENTS NEWS CHANNEL (የተማሪዎች ዜና መስኮት)

#Update
የቀድሞ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታን (ዶ/ር) ጨምሮ 15 ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ

ረቡዕ ግንቦት 2 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የቡሌ ሆራ  ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታን (ዶ/ር) ጨምሮ 15 ተከሳሾች ላይ ከ195 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ የሙስና ወንጀል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ክስ ተመስርቷል።

ተከሳሾቹ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ያለመከሰስ መብታቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተነሳው  በቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታ (ዶ/ር)፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ታምሩ ኦኖሌ፣ የአስተዳደር እና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ሮባ ደንቢ (ዶ/ር)፣ የቢዝነስና ተቋማዊ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አብርሐም ባያብል (ኢ/ር)፣ የግዢ ዳይሬክተር ሊበይ ገልገሎ፣ የግዢ ዳይሬክተር ቦሩ ህርቦዬ፣ የዩኒቨርሲቲው መምህርና የቢኤች ዩ አማካሪ ለታ ድሪባን ጨምሮ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጮችና የቢዳሩ ኮንስትራክሽን ሥራ አስኪያጆች ይገኙበታል።

በተከሳሾቹ ላይ የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ አራት ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክሶችን መመስረቱ ነው የተገለጸው።

በዚህም ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር ያሉት ተከሳሾች የዩኒቨርሲቲው አመራርና የማኔጅመንት አባል በመሆን ሲሰሩ የመንግሥት ግዢ አዋጅን በመተላለፍ በ2012 በያዙት ቃለ ጉባኤ መሰረት ሕግን ባልተከተለ መልኩ ያለአግባብ "ቢኤች ዩ" ለተባለ አማካሪ ግዢው በቀጥታ እንዲፈጸም  በማኔጅመንት ውሳኔ ማስተላለፋቸው ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ውል ሲዋዋል ዩኒቨርሲቲውን በመወከል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት 1ኛ ተከሳሽ ውል ሰጪ ሆነው 7ኛ ተከሳሽ ውሉን በመፈረም በ5ኛ ተከሳሽ ትዕዛዝ መሰረት በአንደኛ ተከሳሽ ሥም ለተመዘገበው አማካሪ ድርጅት ያለአግባብ ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጉን ዐቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል።

በሌላ በኩል  የዩኒቨርሲቲውን የመተዳዳሪያ እና የግዢ አዋጅ በመተላለፍ የ14 ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን  ግዢ በመፈጸምና 116 ሚሊየን 389 ሺሕ 964 ብር ማሽነሪዎችን በስጦታ ያገኙ በማስመሰል ያለአግባብ 12ኛ፣ 13ኛ እና 14ኛ ተከሳሾች በተሽከርካሪ ግዢ ጥቅም ማግኘታቸው ተመላክቷል።

ተከሳሾቹ ሰኔ 10/2012 በቀጥታ ግዢ እንዲፈጸም ውሳኔ በማስተላለፍ ከሌሎች ተከሳሾችና ከሥራ ተቋራጮች ያለአግባብ ካለ ግልፅ ጨረታ ግዢ በመፈጸም በመንግስት ላይ 195 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ በዋና እና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

በዚህ መልኩ የተመሰረተባቸው የክስ ዝርዝርም በችሎት ለተከሳሾቹ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡

ተከሳሾቹ ከጠበቃቸው ጋር ተማክረው የፊታችን ግንቦት 7/2015 ፍድር ቤት ቀርበው ክሱን በንባብ ለማሰማት ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል፡፡

የተጣሩ ተማሪ ነክ መረጃዎችን ለማግኘት ቻናላችንን ይቀላቀሉን
@NATIONALEXAMSRESULT

Click here for advertisement
@studentsnewsadv35bot