🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

የሦስቱ በሬዎች መጨረሻና የእኛ ኢትዮጵያዊያን ነገር..... (በገራዶ ሚዲያ) የተለያየ ቀለም ያ | ገራዶ ሚዲያ

የሦስቱ በሬዎች መጨረሻና የእኛ ኢትዮጵያዊያን ነገር.....

(በገራዶ ሚዲያ)

የተለያየ ቀለም ያላቸው ሦስት በሬዎች (ቀይ፣ ነጭ፣ ጥቁር በሬ) ለአመታት በህብረት/በአንድነት ይኖሩ ነበር። ከዕለታት በአንድ ቀን ምሽት ላይ ሊበላቸው ያሰበ አንድ ጅብ ከሚኖሩበት ቦታ ይመጣል። ነገር ግን እነሱን ለመብላት ሲያስብ ህብረታቸው አስፈራው። አንድ መላም ዘየደ፤ ቀስ አድርጎ እያንዳንዳቸውን ተራ በተራ ለመብላት። ይህ ጅብ ለጥቁሩና ለቀዩ በሬም "ይህ ነጩ በሬ ማታ ላይ ከሩቅ ይታያል፤ አደጋ ያመጣባችኋል። ከእሱ ልትርቁ ይገባል!" ሲል ነገራቸው።

ቀዩና ጥቁሩ በሬም ከነጩ ተነጥለው መኖር ጀመሩ። ጅብም ያንን ነጭ በሬ ብቻውን ስላገኘው በላው፤ ነጩን በሬ በልቶ ሲጨርስም ወደ ቀዩና ጥቁሩ በሬ በመሄድ አሁንም "ይሄ ቀይ በሬ በጨረቃ ሲያዩት ከሩቅ ያብለጨልጫል፤ አደጋ ስለሚያመጣብህ ከእሱ ልትርቅ ይገባል" ሲል ለጥቁሩ በሬ ነገረው።

ጥቁሩ በሬም ከቀዩ በሬ ተነጥሎ መኖር ጀመረ። ጅብም ያንን ቀይ በሬ ብቻውን ስላገኘው በላው፤ ቀዩን በሬ በልቶ ሲጨርስም እነሆ ተራው የጥቁሩ በሬ ነውና ጥቁሩንም በሬ በላው። በሬዎቹም ተበልተው አለቁ።

ከዚህ ታሪክ እንደምንረዳው ጅብ በሬዎቹ በህብረት እንደነበሩ ለመብላት ፈርቶ ነበር። ለመነጣጠል ሞከረ፤ ተሳክቶለት በላቸው። እኛ የተለያየ እምነት፣ ቋንቋ፣ ዘርና የመሳሰሉት ልዩነቶች ያሉን ኢትዮጵያዊያንም ለመነጣጠል የሚመጣን ጠላት አሜን ብለን ከተቀበልን ሁላችንም መጥፋታችን አይቀርም። "ጠላት እኛን ለመብላት ያመቸው ዘንድ መነጣጠልን/መለያየትን ይወዳል!" ከነልዩነቶቻችን በህብረት እንቁም! እንደበሬዎቹ አንሁን! ብሄር፣ እምነት፣ ዘር... ሳንለይ በአንድነት እንቁም። ጠላት አሰፍስፎብናል!

እንደበሬዎቹ እንዳንሆን በህብረት እንቁም!

t.me/geradomedia