2023-05-03 16:33:56
ኦሮሚያ ክልል በደቦ ፍርድ ኢሰብአዊ ድርጊት ፈጸሙ የተባሉ ተያዙ
በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ያቤሎ ወረዳ ሃርወዩ በምትባል ቀበሌ ሁለት ወጣቶች ላይ ኢሰብአዊ ርምጃ የወሰዱ የተባሉ ባለስልጣናት መታሰራቸው ተገለጸ ። በአከባቢው ሰሞኑን ሁለት ወጣቶች እጅ እግራቸውን የፊጢኝ ወደኋላ ታስረው ሲደበደቡና ሲሰቃዩ የሚያሳይ ምስል በማኅበራዊ መገናኛ ተለቅቆ መነጋገሪያ ሆኗል ። ጃሮ ዳሌ እና ጋርቦሌ ዋቆ በተባሉ ሁለት ወጣቶች ላይ የተፈፀመው የደቦ ፍርድ በሚል በሰብአዊ መብት ጥሰት ተተችቷል ።
የያቤሎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጎቡ ጫና በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት፤ በዚህ ሰብአዊ መብትን በጣሰው ድርጊት የተሳተፉት ከቀበሌ አስተዳዳሪ እስከ የአከባቢውን ሰላም እንዲያስጠብቁ የታጠቁ ሚሊሻዎች ያሉት ናቸው ብለዋል ።
በመሆኑም ወጣቶቹን ይዘው ያለ ፍርድ አስረው በማሰቃየት ድርጊት የተጠረጠሩ እስከ ዛሬ የቀበሌ አስተዳዳሪ እና ታጣቂ ሚሊሻዎችን ጨምሮ ዐሥር ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ለፍረድ እየቀረቡ ነው ሲሉ ገልፀዋል ።
አንደ ኃላፊው ገለጻ ለችግሩ መነሻ የሆነው በቀበሌው 6 ኩንታል የርዳታ እህል ጠፍቶ በገበያ መሸጡና በዚህም ስርቆት ሁለቱ ወጣቶች መጠርጠራቸው ነው ። ሁለቱ ለድብደባ እና ስቃዩ የተዳረጉት ወጣቶች አንዱ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ እረኛ ነው ተብሏል ።
የወረዳው አስተዳዳሪ ድብደባው የተፈፀመባቸው ሁለቱ ወጣቶች አሁን በደህና ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙና እነሱን የሚያስከስስ መረጃ አለመኖሩንም አንስተዋል ።
ስለጉዳዩ የተጠየቀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ መረጃ እያሰባሰብኩ ነው ብሏል፡፡
ዘገባ፦ሥዩም ጌቱ ከአዲስ አበባ፤ ዶይቸ ቬለ (DW)
4.1K viewsDW Amharic, 13:33