2021-04-22 09:11:13
"ታጣቂዎች የሴዳል ወረዳን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ተቆጣጥረውታል" - ኢሰመኮ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቤኒንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ ከማሺ ዞን የሚገኘውና ከ25 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የሚገኙበት የሴዳል ወረዳ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ከሚያዝያ 11 ቀን 2013 ጀምሮ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መዋሉን የደረሱት መረጃዎች እንዳመለከቱ አሳወቀ።
ኢሰመኮ ይህን ያሳወቀው ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው።
ኮሚሽኑ በርካታ ነዋሪዎች፣ የወረዳው አስተዳደር እና ፖሊስ አካባቢውን ጥለው ወደ ተለያዩ ስፍራዎች መሸሻቸውን እንደተረዳ ገልጿል።
ታጣቂ ቡድኑ የመንግስትና የግለሰብ ንብረቶችን ማቃጠሉን፤ ነዋሪችን፣ የወረዳውን እና የዞን አመራሮችን እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞችን መግደሉን እና ማገቱም ተገልጿል።
ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በአቅራቢያው ያለው የፀጥታ ኃይል ከአቅሙ በላይ እንደሆነና ተጨማሪ የተላከው ኃይልም ወደ አካባቢው እንዳልደረሰ ገልፀዋል።
ይህ ክስተት በክልሉ የቆየው የጸጥታ ችግር እየተባባሰ እና መልኩን እየቀየረ መምጣቱን የሚያሳይ በመሆኑ ከፍተኛ ስጋት የሚያሳድር ነው ብሏል ኢሰመኮ።
ኮሚሽኑ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን በመግለፅ፥ ከሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል መንግስት አካላት ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑን አሳውቋል።
ኢሰመኮ መንግስት በአፋጣኝ የአካባቢውና የክልሉን የፀጥታ ኃይል እንዲያጠናክርና እና ተጨማሪ የሰዎች ሞትና የከፋ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዳይከሰት እንዲከላከል ጥሪ አቅርቧል።
t.me/geradomedia
397 viewsGashu, 06:11