2021-02-13 21:24:06
#የትግራይ_ክልል_ወቅታዊ_ሁኔታ
በመቐለ ከተማ 80% የመንግስት መስሪያ ቤቶች ወደ ስራ መመለሳቸው፦በመቐለ ከ80 በመቶ በላይ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ወደመደበኛ ስራ መመለሳቸውን እና ህዝቡን ማገልገል እንደጀመሩ የመቐለ ከተማ የመንግስታዊ አገልግሎት ገልጿል።
የከተማው የመንግስት አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ መምህር ገብረኪሮስ ህሉፍ፥ "በገጠመው የመፀጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ቁሳቁሶች በመውደማቸው ምክንያት እስካሁን አገልግሎት መስጠት ያልጀመሩ የተወሰኑ መስሪያ ቤቶች እንዳሉ ገልፀው መስሪያ ቤቶቹ ወደስራ እንዲመለሱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አሳውቀዋል።
በየመስሪያ ቤቱ ኮፒዩተር፣ የፅህፈት መሳሪያ የመሳሰሉት ወድመዋል፤ ተዘርፈዋል። የጠፉ ንብረቶች ተጠንተው ወደሚመለከተው አካል ሪፖርት መደረጉን እና ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በመሆን አስፈላጊውን ቁሳቁስ ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን መምህር ገብረኪሮስ ህሉፍ ተናግረዋል።
የትግራይ መልሶ ማቋቋም ስምምነት ከUNDP ጋር፦በትግራይ መልሶ ግንባት ላይ ድጋፍ ለማድረግ UNDP ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሰተዳደር እና ከኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር በትግራይ ያሉ ተቋማት የመለሶ ግንባታ ስራ ተጠናቆ በቅርቡ ሁሉም ስራ እንደሚጀምር አሳውቋል።
በትግራይ ክልል ግብር የመሰብሰብ ጉዳይ፦
ከትግራይ መልሶ ማቋቋም ጎን ለጎን ግብር የመሰብሰብ ስራ እንደሚቀጥል የክልል ትግራይ ጊቢዎች ባለስልጣን አሳውቋል።
የክልል ትግራይ ገቢዎች ባለስልጣን በመቐለ ካለው የተሻለ ሰላም እና ፀጥታ አንፃር ሁሉንም ፅ/ቤቶቹን ከፍቶ መደበኛ ስራ መጀመሩን ገልጿል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምንም እንኳን በመቐለ እንደመነሻ መደበኛ ስራውን ቢጀምርም በዞን እና በወረዳ ካለው ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በሚደረግ ውይይት ከሌሎች መስሪያ ቤቶች ጎን ለጎን ፅ/ቤቶቹ እንዲከፈቱ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አሳውቋል።
ሰላም ሚኒስቴር የሚደረገው ድጋፍ መቀጠሉን ማሳወቁ፦በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ስርጭት እስከ አሁን በ32 ዞኖችና ወረዳዎች በሚገኙ 92 የስርጭት ጣቢያዎች ተጠናክሮ መካሄዱን ቀጥሏል ሲል አሳውቋል።
በተመሳሳይ ድጋፉ በክልሉ በሚገኙ ሁለት የስደተኞች መጠለያ ካምፖች እየተዳረሰ እንደሚገኝ ገልጿል።
በትግራይ የቀጠለው አድማ እና ተቃውሞ የሰዎችን ህይወት መቅጠፉ፦
በትግራይ ክልል ግፍ እየተፈፀመ፣ የሃይማኖት መሪዎች እየተገደሉ፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉዳት እየደረሰባቸው ባለበት ወቅት የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ድርጊቱን ሳያወግዙ ወደ ትግራይ ክልል መምጣታቸው ትክክል አይደለም በሚል ምክንያት የተነሳው ተቃውሞ/አድማ በተለያዩ ከተሞች ቀጥሏል።
ተቃውሞው ከመቐለ ጀምሮ ወደ ውቅሮ፣ ፈረወይኒ፣ እዳጋሃሙስ፣ ዓዲግራት፣ አድዋ፣ ሽረ ፣ አክሱም ከተሞች ነው የተስፋፋው።
በከተሞቹ የሃማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማጌዎች መጥተዋል በሚል ነው ተቃውሞ የተነሳው። በመቐለ በተቃውሞ እና አድማ ተቋርጦ የነበረው እንቅስቃሴ ከትላንት ጀምሮ ወደመደበኛው ሁኔታ ተመልሷል።
የትራንስፖርት (ታክሲ አገልግሎት) ጀምሯል፣ ንግድ ተቋማት፣ አገልግሎት ሰጪዎች ተከፍተዋል መደበኛ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ተመልሷል።
በአክሱም ከሀሙስ ጀምሮ ነው ተቃውሞ የተቀሰቀሰው፤ ተቃውሞው የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት መሪዎች ገብተዋል በሚል የተቀሰቀሰ ሲሆን መንገድ የመዝጋት፣ ጎማ የማቃጠለ ሁኔታዎች እንደነበሩ ተሰምቷል።
እያሱ ተስፋይ የተባሉ የከተማው ነዋሪ ትላንት ምሽት በነበረው የአሜሪካ ድምፅ የሬድዮ ጣቢያ መደበኛ ስርጭት አማርኛው ክፍል በሰጡት መረጃ በተነሳው ተቃውሞ የመከላከያ እና የኤርትራ ኃይል ተኩስ በመክፈቱ 7 ሰዎች መሞታቸውን እና 4 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልፀዋል። በ3ቱ ሰዎች ቀብር ላይም እንደነበሩ አሳውቀዋል።
የኤርትራ ሰራዊት በከተማው ስለመኖሩ በምን እንደለዩ የተጠየቁት የከተማው ነዋሪ የሚጠቀሙበት መኪና የኤርትራ ታርጋ ያለው መሆኑን እና በሚለብሱት መለዮ እንደሚለዩ ገልፀዋል።
በውቅሮ ከተማ በነበረው ተቃውሞ 17 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉትን ኣንዲት የከተማው ነዋሪ ተናግራለች።
ይህች መረጃውን የሰጠች የወቅሮ ከተማ ነዋሪ ሁለት ጎረቤቶቿ ከሟቾች መካከል እንደሚገኙ ገልፃለች።
በከተማዋ መንገዶች በተዘጉበት ወቅት መንገዶችን ክፍቱ በሚል ነበር ተኩሱ የተከፈተው ፤ የተኩሱንም ድምፅ ሰምተው ይሮጡ የነበሩ ሰዎችም በጥይት ተመተው መገደላቸውን ተናግራለች።
በሽረ እንደስላሴ ከተማ በተቃውሞ ምክንያት በተተኮሰ ጥይት 4 ሰዎች መሞታቸውን ወልደስላደ መኮንን የተባለ የከተማው ነዋሪ ተናግሯል።
በከተሞቹ የትራንስፖርት መቋረጥ፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መዘጋት አድማ እንደትላንት ድረስ ቀጥሎ መዋሉን ጋዜጠኛ ሙልጌታ አፅብሃ ዘግቧል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኢተነሽ ንጉሰ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑና ስለተፈጠረው ሁኔታ ሙሉ መረጃ እና ማብራሪያ እንደሚሰጥ ገልፀዋል።
የዶክተር ሙሉ ነጋ ከኢዜአ ጋር የነበራቸው ቆይታ፦
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ በክልሉ ባለፉት ሁለት እና ሶስት ቀናት ስለነበረው ሁኔታ ግልፅ ማብራሪያ ባይሰጡም የትግራይ ክልል ወጣቶች መጻኢ ዕድላቸው ብሩህ እንዲሆን ለጥፋት ቡድኑ ተላላኪ ከመሆን መቆጠብ አለባቸው ብለዋል።
ዶ/ር ሙሉ፥ የጥፋት ቡድኑ ርዝራዦች በክልሉ ሕዝብ ላይ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ጉዳት እንዲደርስ እያካሄዱት ላለው ቅስቀሳ ወጣቱ ተሳታፊ ባለመሆን ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ነው ጥሪ ያቀረቡት።
ወጣቱ የጥፋት ቡድኑ ርዝራዦች በክልሉ ሠላምና መረጋጋት እንዳይኖር ከውጭ አገር ሆነው የሚያስተላልፉትን የግጭት መልዕክት ዓላማ በአግባቡ ሊረዳው ይገባል ሲሉም ነው የገለፁት።
ዶ/ር ሙሉ ነጋ፥ "በአሁኑ ወቅት ወጣቱን የሚጠቅመው የሥራ ዕድል ማግኘትና ራሱን መቻል በመሆኑ ለጥፋት ተግባር ተባባሪ መሆን የለበትም"
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሕዝቡን ኑሮ ወደኋላ ለመመለስ እየተደረገ ያለው ያልተገባ ተግባር ትክክል አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የጥፋት ቡድኑን ለመመለስ ማሰብና ለዚህም ጊዜ ማጥፋት ፋይዳ የሌለው ከመሆኑ በላይ ወጣቱን ስለሚጎዳ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ዶክተር ሙሉ አሳስበዋል።
Via Tikvaht.me/geradomedia
7.9K viewsGashu, 18:24